Sunday, August 2, 2015

ጵራቅሊጦስ በሚለው ቃል የተሰራው “ግፍ” ሲገለጥ፡-

          <<ጵራቅሊጦስ>> በሚለው ቃል የተሰራው “ግፍ” ሲገለጥ፡-

    በ2000 ዓ/ም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ያሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ በ1ዮሐ2፡-1 ላይ ያለውን ቃል እንዲህ በማለት ነው የተጻፈው፡-
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፡-1 “ልጆቼ ሆይ፥ እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ <<ጵራቅሊጦስ>> አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢያታችንን ያስተሰረይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፡፡” <<ጠበቃ>> የሚለውን የአማርኛ ቃል ቀይረው በምትኩ ደግሞ የግሪኩን ቃል <<ጵራቅሊጦስ>> //parakletos// የሚለውን ተጠቅመዋል፡፡ በግርጌ መግለጫው ላይ ያሰፈሩትም <<የግሪኩ፡- ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ “ጵራቅሊጦስ” አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።>> በማለት ብቻ ነው ያስቀመጡት፡፡ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የምስኪኑን ሕዝብ ማዕከል ያደረጉ 2 የተፈጸሙ አበይት ስህተቶች እንመልከት፡-
1ኛ/ የመጀመርያው ስህተቱ “ጵራቅሊጦስ” የሚለው ቃል “ገላጭነቱ” ወይም “አስረጅነቱ” ለኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ በመቀየር ለመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ተደርጎ መጻፉ ነው፡፡ ይህም “ጵራቅሊጦስ” የሚለው ቃል መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በቤተክርስቲያኒቱ ስር የሰደደ ትምህርት ከመኖሩ ጋር በማያያዝ፤ ከአብ ዘንዳ መንፈስ ቅዱስ ነው ያለው የሚል ድምዳሜን በመስጠታቸው ነውና፤ የክርስቶስን ዘላለማዊ የሊቀ ካህንነቱን አገልግሎት ለመሸፈን የተደረገ ስልታዊ ኑፋቄ ነው፡፡ ነገር ግን “ጵራቅሊጦስ” የሚለው የግሪኩ ቃል ሕይወት ያለው የአካላዊው መንፈስ ቅዱስ የስም መጠሪያ ሆኖ ሳይሆን የተጻፈው፤ ይልቁንም <=== የመንፈስ ቅዱስን የሥራ ድርሻ ወይም በክርስቶስ የሆኑትን አማኞች በሙሉ የሚያጽናና መሆኑን===> የሚገልጥ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም በአማርኛ <<አጽናኝ፣ ጠበቃ፣ አማላጅ፣ ወኪል>> እንደማለት ማለት ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ቃል በ“strong’s Hebrew And Greek dictionary” ላይ በማመሳከር ማየት ይሆናል፡-
1John 2፡-1 “My little children, these things write I unto you, that ye sin not. And if any man sin, we have an <<ADVOCATE>> with the Father, Jesus Christ the righteous” KJV. በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ <<ጵራቅሊጦስ>> የሚለው ቃል በኢንግሊዘኛው <<ADVOCATE>> የሚለውን አቻ ቃል የያዘ ነው፡፡
1John 2፡-1 “ My<3450> | little children<5040>, | these things<5023> | write I<1125> | unto you<5213>, | that<2443> | ye sin<264> | not<3361>. | And<2532> | if<1437> | any man<5100> | sin<264>, | we have<2192> | an advocate<3875> | with<4314> | the Father<3588><3962>, | Jesus<2424> | Christ<5547> | the righteous<1342>” በዚህም መሰረት
<<ADVOCATE>> የሚለው ቃል ወደ “strong’s Hebrew And Greek dictionary” የማመሳከሪያ ኮዶች ስናይ በቁጥር “an advocate<3875>” የተመለከተው ሲሆን፤ በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ጵራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ሲተረጉም እንዲህ የሚል ትርጉም አለው፡-
=== <<3875 parakletos, par-ak'-lay-tos>> “AN INTERCESSOR, CONSOLER, ADVOCATE , COMFORTER” የሚል የቃል ፍቺ ነው የሚሰጠው፡፡ በዚህም መሰረት “ጵራቅሊጦስ” የሚለው ቃል <<አማላጅ፣ ጠበቃ፣ አጽናኝ፣ ወኪል>> ማለት ነው እንጅ የአካላዊው መንፈስ ቅዱስ የስም መጠሪያው አይደለም፡፡ ሙሉ በሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታ ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ እንደርሱ ያለ ሌላ አጽናኝ ከእነርሱ ጋር እንዲኖር ወደ አባቱ እንደሚጸልይ በገለጠ ጊዜ፤ “አጽናኝ” ወይም በግሪኩ “ጵራቅሊጦስ” የሚለውን ቃል “የአካላዊውን የመንፈስ ቅዱስ” ስም መጠሪያ እንደሆነ አድርጎ ሳይሆን የተጠቀመበት፤ ይልቁንም ደቀመዛሙርቱን የሚያበረታ፣ የሚያጽናና፣ የሚደግፍ፣ ከአብ ዘንድ እንደሚመጣና በተስፋ እንዲጠብቁ የሚያበረታታ ቃል አድርጎ መናገሩን ማስተዋል ከበቂ በላይ ነው፡- በዮሐ14፡-15/16 “ብትወዱኝ ትዕዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር “ሌላ” <<አጽናኝ>> ይሰጣችኋል፡፡” ሌላው በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ===የአካላዊው መንፈስ ቅዱስ=== የስም መጠሪያን ማውቁ ያስፈልጋል፣ ይህም በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን ማቴ28፡-19 ላይ <<መንፈስ ቅዱስ>> ብለን እንደምንጠራው በግሪኩ ደግሞ በ“strong’s Hebrew And Greek dictionary” ስናመሳክረው “4151 pneuma, pnyoo'-mah” የሚል የስም መጠሪያ ነው ያለው፤ እንጅ “parakletos” አለማለቱን ልብ ይሏል፡፡ እንግዲህ በግልጥ እንዳየነው “ጵራቅሊጦስ” የሚለው ቃል የኢየሱስንና መንፈስ ቅዱስን ሥራ/ግብር/ የሚገልጥ ገላጭ ቃል (በዮሐ14፡-15/16) እንጅ የመንፈስ ቅዱስ የመጠሪያ ስም አይደለም፡፡ በመሆኑም በ1ዮሐንስ መልዕክት 2፡-1 ላይ ያለው ቃል ስለ መንፈስ ቅዱስ አንዳች የሚያወራ ሃሳብም ይሁን ዘይቤ ሊኖረው ይቅርና የሚያስጠረጥርም ነገር የለውም፡፡ የዮሐንስ መልዕክት አውዳዊ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ የሚያመለክተውና የሚያውጀው ክርስቶስ ኢየሱስን ብቻ ነው፡፡
2ኛ/ ሁለተኛው ስህተት “ጵራቅሊጦስ” የሚለውን ቃል በቀጥታ ከግሪኩ ወስደው ለመጽሐፉ ሲጠቀሙ በግርጌ መግለጫ ላይ፤ ቃሉን ካለምንም ትርጉምና <<የአማርኛ አቻውን ቃል>> ለምን ሳይጠቀሙ እንደቀሩ፤ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ሳይሰጡ የማለፋቸው ምስጢር ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው ሐዋርያቱ አዲስ ኪዳንን በጻፉት የግሪኩም ይሁን በኢንግሊዘኛው KJV እንደገናም ደግሞ በ1954 ዓ/ም የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን እንዳረጋገጡልን “ጵራቅሊጦስ” የሚለው ቃል <<አማላጅ፣ ጠበቃ፣ አጽናኝ፣ ወኪል>> ማለት እንደሆነ አይተናል፡፡ በ2000ዓ/ም ላይ በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ጵራቅሊጦስ” ለሚለው የግሪኩ ቃል የአማርኛ አቻ ቃሉን እንደአውዱ ሲተረጎም <<ጠበቃ>> የሚለው ቃል ሊቀመጥ እንሚገባ አጠውት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትጠቀምበት የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት መጽሐፍ ላይ “ጵራቅሊጦስ” የሚለውን የግሪኩን ቃል ሁለት ፍቺ የሰጡት ሲሆን፣ የመጀመርያው፡- <<አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ ትርጁማን፣ አምጃር፣ እያጣፈጠ የሚናገር፣ ስብቅል ከአፉ ማር ጠብ የማይል>> በማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፡- <<ናዛዚ መጽንኢ፣ መስተፍሥሒ፣ መንፈስ ቅዱስ፡፡ በዓለ ሃምሳ፣ ትንሳኤ ዐምሳኛ፣ የዕርገት ዐሥረኛ፣ እሁድ ቀን የሚውል>> የሚል ነው፣ መዝገበ ቃላት (1948// 907) ላይ ይመልከቱ፡፡ በ1ዮሐ2፡-1 በግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንዲህ ነው፡-
“ደቂቅየ ዘንተ እጽሕፍ ለክሙ ከመ ኢትአብሱ ወእመኒ ቦ ዘአበሰ <<ጵራቅሊጦስ>> ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ ውእቱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ ወአኮ በእንቲኣነ ባህቲቱ አላ በእንተ ዓማኒ”
ለዚህም ቃል የአማርኛ ትርጉም የተሰጠው እንዲህ የሚል ነው፡- “ልጆቼ ሆይ፥ እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ <<ጵራቅሊጦስ>> አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢያታችንን ያስተሰረይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፡፡” እኝህ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ወእመኒ ቦ ዘአበሰ <<ጵራቅሊጦስ>> ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ” ለሚለው የግዕዝ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ሲያመጡ የሰጡት አቻ ቃል ከላይ እንዳየነው የመጀመርያውን ትርጉም ነው፡፡ ይሄውም <<አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ “ጠበቃ”፣ ትርጁማን፣ አምጃር፣ እያጣፈጠ የሚናገር፣ ስብቅል ከአፉ ማር ጠብ የማይል>> የሚለውን ትርጉም ነው፡፡ በመሆኑም <<ጵራቅሊጦስ>> የሚለው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን እንጅ መንፈስ ቅዱስን እንደማያመለክት ገልጠዋል፡፡ በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም <<ጵራቅሊጦስ>> የሚለውን የግሪክ ቃል በአማርኛ አቻ ቃሉ <<ጠበቃ>> መባሉ ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ማወቅ በቀላሉ እንችላለን፡፡
ወዳጆቼ በእነዚህ ሁለት አበይት ስህተቶች የደረሰው ነገር በሕዝቡ ላይ ሞት ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስን ዘለዓለማዊ የሆነውን የሊቀ ካህንነት ሥራ ክዶ ጽድቅ የሚባል ነገር የለምና፡፡ ታዲያ ለምን ይሄን አይነት ክህደት መፈጸሙ አስፈለ ስንል፡- በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ያሉ የክርስቶስ ወንጌል ተቃዋሚዎች፣ የክርስቶስን ዘላለማዊ የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ክደው ምስኪኑን ህዝብ ለማስካድ ምንም አይነት ርህራሄ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ ለምስኪኑ ህዝብ ምንም አይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ <<በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሞት ደብዳቤ የሚጽፉ>> ለዲያብሎስ ሃሳብ የወገኑና ልባቸውን ለድቅድቅ ጨለማ ያስማረኩ ሐኬተኞች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በጨለማ ለሚወነባበደው፣ ማረፊያ እንዳጣች ወፍ ለሚቅበዘበዘው ምስኪን ሕዝብ፣ እውነቱን እየገለጠለት ከዘለዓለማዊው ሞት ያመልጥ ዘንድ፣ እኛ ግን የክርስቶስ ሕይወት እጅግ በዝቶ የተትረፈረፈልን ክርስቲያኖች በብርቱ እንጸልያለን፡፡
ተሐድሶ ለአርቶዶክስ!!
https://www.facebook.com/groups/705796459440764/permalink/967146109972463/ 

No comments:

Post a Comment