Tuesday, August 11, 2015

5ቱ የጥምቀት ዓይነቶች

ንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና(ዕብ.6፡2)
ጥምቀቶች የሚለው ብዙ ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ጥምቀቶች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ የሚከተሉትን መዘርዘር ይቻላል፡፡

1.የአካል ጥምቀት

…እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና…
(1ኛ ቆሮ.12፡13)፡፡ አጥማቂ መንፈስ ቅዱስ ሲሆን መጠመቂያው የክርስቶስ አካል ነው፡፡ …ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን …(ሮሜ.6፡2) ሲል ይህንን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ለመዳን ብቸኛው አስፈላጊ ጥመምቀት ነው ይህ ጥምቀት፡፡ ባመንን ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ አካል ይጨምረናል፤ ኤፌ.1፡13 እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ ይለናል፡፡ የኤፌ.4፡4-5 ሀሳብ የውሀ ጥምቀት ሳይሆን ይህ ነው፡- አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት የተባለው፡፡

2.የውሀ ጥምቀት

 በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።
ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።
ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። (የሐዋ.8፡36-38)
አጥማቂው አገልጋይ ሲሆን መጠመቂያው ውሀ ነው፡፡ ይህ ለንሰሐ(ማቴ.3፡11፤ዮሐ.4፡1-2) እና ለበጎ ህሊና ልመና(1ጴጥ.3፡21) ነው፡፡ ምሳሌአዊ አገልጎሎት እንጂ የማዳን ጉልበት የለውም፡፡ ጌታ በዮሐ.3፡5 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ያለው ከውሐ መወለድን ከመንፈስ መወለድ ጋር አቆራኝቶ ነው፡፡ ስለዚህ የውሀ ጥምቀት ንሰሐን ያመለክታል፡፡ ማመን ይቀድማል፣ በውሀ መጠመቅ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ነው ማር.16፡16 ያመነ የተጠመቀም ይድናል የሚለን፡፡

በማን ሥም እንጠመቅ?
የተልዕኮ ሥልጣንን በተመለከተ ማቴ.28፡18-19  ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው… ሲለን አጥማቂው አገልጋይ በሥላሴ ሥልጣን ስር ሆኖ እንዲያጠምቅ መታዘዙን ያመለክታል፡፡ የሐዋ.2፡38 ደግሞ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ…ሲል ተጠማቂው በኢየሱስ ሥም በመማመንና ንሰሐ በመግባት እንደሚጠመቅ ያሳያል፡፡
ስለዚህ በማን ሥም እንጠመቅ ለሚል የ Jesus only አማኞች ጥያቄ መልሱ እንደሚከተለው ይሆናል፡- አጥማቂው የሥላሴን ሥም እየጠራ ያጠምቃል፤ ተጠማቂው ደግሞ የኢየሱስን ሥም እየጠራ ይጠመቃል፡፡ ስለዚህ በማን ሥም እንጠመቅ ለሚለው አብሮ በማን ሥም እናጥምቅ የሚለውም መነሳት አለበት፡፡ ማጥመቅ( βαπτίζοντες ባፕቲዞንተስ) እና መጠመቅ (βαπτισθήτω ባፕቲስዜቶ) የተለያዩ የአንድ ቃል እርባታዎች ናቸው፡፡

3. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት

ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ (የሐዋ.1፡5)
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ (የሐዋ.1፡8)
እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል (ማቴ.3፡11)
አጥማቂው ኢየሱስ ሲሆን መጠመቂያው መንፈስ ቅዱስ  ነው፡፡ አስፈላጊነቱ ለአገልግሎት ኀይልና የተለያዩ ፀጋ ስጦታዎችን ለመቀበል ነው፡፡ በበዓለኀምሳ ቀንም የሆነው አስረጂ ነው፡፡ በውሐ ዕንዲጠመቁ የተነገራቸውም ይህንን ስጦታ ማግኘት እንደሚችሉ የዘር ዘራቸው እና በሩቅ ያሉም የዚሁ እድል ተጠቃሚ ዕንደሚሆኑ የተነገራቸው እንዲህ በማለት ነው፡-  
የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና (የሐዋ.2፡38-39)፡፡ 1ኛ ቆሮ. 12 የሚከተለውን ይለናል፡-
7 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል።
8 ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥
9 ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥
10 ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤
11 ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።

4. የእሳት ጥምቀት

እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል (ዮሐ.3፡11)፡፡
ሁለት የተለያዩ ጥምቀቶች ናቸው የተጠቀሱት፡፡ የመንፈስ ጥምቀትን ተነጋግረንበታል፡፡ አብሮ የተጠቀሰው የእሳት ጥምቀት ነው፡፡ አጥማቂው ጌታ ነው፤ መጠመቂያው ደግሞ መንፈሳዊ እሳት፡፡ አስፈላጊነቱን በተመለከተ ቀጥር 12 ላይ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል ይለናል፡፡ ህይወትን የሚያጠራ እሳት ነው፡፡ በሚልክያስ መጽሐፍ መዕራፍ 3 ላይ ጥሩ ትንቢታዊ ማስረጃ አለን፡-
1፤ እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
2፤ ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው?
3፤ እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።
4፤ እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል፡፡
                 
5. የመከራ ጥምቀት

 ኢየሱስም እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ ሲል ለዘብዴዎስ ለጆች የተናገረው ነው (ማር.10፡39)፡፡

አጥማቂ አልተጠቀሰም፡፡ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ መጠመቂያው መከራ ነው፡፡  አስፈላጊነቱ ለብስለት (ያዕ.1፡2-4) ወይም በጥበብ ለማደግ እና መታዘዝን ለመማር (ያዕ.1፡5፤ዕብ.5፡8-9፤ሉቃ.2፡52) እንዲሁም ለባህሪ መታነጽ ነው(ሮሜ.5፡3-4)፡፡

http://restorers.page.tl/%26%234768%3B%26%234637%3B%26%234661%3B%26%234725%3B-%26%234768%3B%26%234845%3B%26%234752%3B%26%234725%3B-%26%234901%3B%26%234637%3B%26%234672%3B%26%234726%3B%26%234733%3B.htm

No comments:

Post a Comment