Thursday, July 30, 2015

የኢየሱስ ክርስቶስ ጌታነት


                     አዲስ ኪዳን ኢየሱስን ጌታ ብሎ ሲጠራው፣ ኪዩሪየስ (Kurios) የተሰኘውን የግሪክ ቃል ፍቺ ይይዛል፡፡ ኪዩሪየስ (Kurios) ገዢ ወይንም ጌታ የሚለውን የተለመደ ቃል ፍቺ ይይዛል፣ ይህም የእንግሊዝኛው ቃል ጌታዬ (Sir) በማለት አገልግሎት ላይ የሚያውለውን የአክብሮት መጠሪያም ይዞ ያገለግላል፡፡ ለነገሩ፣ ኪዩሪየስ የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጊዜ ለሰብዓዊ ሰዎችም አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 24፣ ሉቃስ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 36 እስከ 47፣ ኤፌሶን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 5 እስከ 9 እና በሌሎችም በርካታ ስፍራዎች እናገኘዋለን፡፡ በተመሳሳይም፣ አዲስ ኪዳን ኪዩሪየስ የሚለውን ቃል የእግዚአብሔር ስም አድርጎም ተጠቅሞበታል፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 11 ቁጥር 25፣ ሉቃስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 16፣ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 39 እና በሌሎችም በርካታ ምንባቦች እናገኘዋለን፡፡ ይህንን ሰፊ አፈታት ከተመለከትን፣ በአዲስ ኪዳን ኪዩሪየስ የሚለው ቃል የኢየሱስን መለኮትነት ያመለክታል ብለን ለምን እናስባለን? ለምንድን ነው ቃሉ በምድር ያለውን ሥልጣንና ክብር ብቻ ለማመልከት የማንጠቀምበት? ብለን መጠየቅ መልካም ነው፡፡ የክርስቲያኖች ኪዩሪየስ የሚለው ቃል አጠቃቀም ቁልፉ ብሉይ ኪዳን ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በዕብራይስጥ ነው፡፡ ሆኖም፣ ክርስቶስ ከመወለዱ ጥቂት ምዕተ-ዓመታት ቀደም ብሎ፣ የዕብራይስጡ ቅጂ ወደ ግሪክ ተተረጎመ፡፡ ይህም ትርጉም Septuagint ሰብዓ ሊቃናት በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ የአይሁድ ምሁራን ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ሲተረጉሙ፣ ኪዩሪየስ የሚለውን የግሪክ ቃል 6700 ጊዜ ያህል እግዚአብሔር ለህዝቡ ራሱን የገለጠበትን ያህዌ (Yahweh) የተሰኘ ቅዱስ ስም ለመተርጎም ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ የቀደምት ታሪክ ማስታወሻ አዲስ ኪዳን ለኢየሱስ ያዋለውን የኪዩሪየስ ፍቺ ለመረዳት ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ምንም እንኳን ኪዩሪየስ የሚለው ቃል በራሱ የኢየሱስን መለኮትነት ባያስረዳም፣ የዚህ ቃል የብሉይ ኪዳን ቀደምት ታሪክ ማስታወሻ በርካታ ምንባቦች ውስጥ የኢየሱስን መለኮትነት በግልጥ እንዲያመለክት አድርጎታል፡፡ በአዲስ ኪዳን ከምናገኛቸው አስደናቂ ምንባቦች አንዱ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ (ፊልጵስዩስ 2፥10-11) በመሠረቱ፣ ጳውሎስ፣ በዚያን ወቅት የጠቀሰው ከኢሳያስ ነው፣ ያም ያህዌ ጌታ ነው ብሎ እያንዳንዱ ሰው የሚያውጅ መሆኑን የሚገልጥ ዝማሬ ነው፡፡ እርሱም ን ብሎ የብሉይ ኪዳኑን ምንባብ ወስዶ ያንኑ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው ብሎ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚያም ወቅት አዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያው ምድራዊ ጌታ ብቻ ሳይሆን፣ ከእስራኤል ጌታ አምላክ ጋር አንድ እንደሆነ በግልጽ ያመለክት እንደነበር እውቅ ነበር፡፡ እስኪ ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 10 ቁጥር 9እና 13 ላይ የጻፈውን አድምጡ፡ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤… የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። በቁጥር 13 ላይ ጳውሎስ የሚያጣቅሰው ከኢዩኤል ምዕራፍ 2 ቁጥር 32 ሲሆን ይህንንም የኢየሱስን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል የሚለውን ለማረጋገጥ ተጠቅሞበታል፡፡ ከኢዩኤል የተጠቀሰው ጥቅስ በብሉይ ኪዳን፣ ጌታ የሚለው ስም ያህዌ፣ አግባብነት ያለው የእግዚአብሔር ስም መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ በቀላሉ ስናስቀምጠውም፣ ጳውሎስ ኢየሱስ ጌታ ነው ሲል፣ ኢየሱስ ያህዌ፣ የብሉይ ኪዳኑ ጌታና አምላክ ነው ማለቱ ነው፡፡ኢየሱስን ከብሉይ ኪዳኑ አምላክ ጋር የሚያስተካክሉት የአዲሰ ኪዳን ምንባቦች ማቴዎስ ምዕራፍ 3፣ ማርቆስ ምዕራፍ 1፣ ሉቃስ ምዕራፍ 3 እና ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ሲሆኑ በዚያም ኢየሱስ በኢሳያስ ምዕራፍ 40 የተጠቀሰውና መጥምቁ ዮሐንስም መንገዱን የጠረገለት ጌታ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ተመሳሳዩን መግለጫ በዕብራውያን ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 ላይ ጌታ ኢየሱስ በመዝሙር 102 ከቁጥር 24 -25 ዓለምን የፈጠረ ተብሎ የተጠቀሰው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዝርዝሩ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡ እንግዲህ፣ በአዲስ ኪዳን ሰዎች ኢየሱስን “ጌታ” ሲሉት ዘወትር መለኮትንቱን ማመልከታቸው ነው እያልን አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰብዓዊ ከበሬታን ሊሰጡትም ሲሹ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ልክ እኛ በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ እንደምናደርገው ስታውጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ፣ በአምላክነቱም የስላሴ ምሉዕ አባል፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ እኩል መለኮታዊ የባህርይ መገለጫዎች ያሉት ነው የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ማረጋገጣችን ነው፡፡ የክርስቶስ መለኮትነት ለክርስትና ሕይወት ሁሉን ዓይነት እንድምታ አካትቷል፡፡ ለምሳሌ፣ በጸሎቶቻችንና በዝማሬዎቻችን ሁሉ ኢየሱስን እንደ አምላክ ልናመልከውና እውቅና ልንሰጥ የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ትምህርት ሦስት/APC3 ኢየሱስ ክርስቶስ 12 ይገባናል ማለት ነው፡፡ ልክ ወደ አብና ወደ መንፈስ ቅዱስ እንደምጸልይ ሁሉ ወደ እርሱምእንጸልያለን ማለት ነው፡፡ እናም እግዚአብሔር ራሱ ከኀጢአት እንደዋጀን በማወቅ ከድነት ዋስትናችን አንፃር ትልቅ መጽናናትንና እርግጠኝነትን እንይዛለን ማለት ነው፡፡ እነዚህና ሌሎችም በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የሚያርፉት በክርስቶስ መለኮትነት ባለን እምነት ላይ ነው፡፡ ይህንን የኢየሱስን መለኮትነት በልቡናችን ይዘን፣ በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ውስጥ የእርሱ ሰውነት የተንፀባረቀበትን መንገድ ወደ መመልከቱ እንሻገራለን፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮትነት



ስለ ክርስቶስ መለኮትነት ስንነጋገር፣ ወይም በተሻለ አግባብ፣ ስለ አምላክነቱ ስንነጋገር ማለትም እርሱ ፍፁም አምላክ የመሆኑን እውነታ ስንጋገር አዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ማንነት የሚያነሳውን ማረጋገጫ ማለታችን ነው፡፡ የተነገረንም ኢየሱስ ፍፁም አምላክ ፍፁምም ሰው መሆኑን ነው፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ ዘወር ባልንበት ቅጽበት ኢየሱስ የለንም ማለት ነው፡፡ ኢየሱስን ከአምላክነቱ አንፃር ልንገልጥ የምንችልበት ብቸኛ መንገድ መጽሐፍ ቅዱሱ በገለጠው መንገድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የነገረን እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ነው፡፡ በመጀመሪያዪቱ ቤተክርስቲያን ይሰበክ የነበረውመሠረታዊ እውነታ ይህ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች ከፃፈው እንደምንመለከተው ያለን ዋስትና ኢየሱስ በሁሉም ላይ ትልቅ ሥልጣን ያለው መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም በእርሱ ተፈጥሯል፡፡ ሥልጣን ሁሉ በእግሩ ስር ይሰግዳል፡፡ ይህም የተነገረው ለአምላክ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካወጣን፣ ወንጌል የለንም፣ ኢየሱስም የለንም ክርስትና ብሎ ነገርም የለም፡፡ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ መለኮትነት የሚያነሳው በእነዚህ ቃላት ነው፡ 
…በአንድ ልጁ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፡፡ ክርስቲያኖች ዘወትር “ክርስቶስ”፣ “የእግዚአብሔር ልጅ” እና “ጌታ” የሚሉትን ቃላት ለኢየሱስ መለኮትነት ይጠቀማሉ፡፡ ለአሁኑ ዓላማችን ግን፣ ሐዋርያት የኢየሱስን መለኮትነት ለማመልከት በተጠቀመባቸው ሁለት ቃላት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ በአንድ ወገን፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑን እውነታ እንመለከታለን፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንመረምራለን፡፡ እስኪ ቅዱሳት መጻሕፍት ለኢየሱስ የተጠቀሙበትን “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለውን ቃል ፍቺ በመመልከት እንጀምር፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ 
“የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለውን ቋንቋ አስመልክቶ ልናስታውሰው የሚገባ የመጀመሪያ ነገር ይህንን ቃል መለኮትነት ለሌላቸውም አካላት ጭምር ቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቀመውበት እንደነበር ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እንደ ኢዮብ ምዕራፍ 1 ቁጥር 6 እና ምዕራፍ 2 ቁጥር 1 ያሉትን ምንባቦች ስንመለከት መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ በጥቂት ዘመናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ጥቅሶቹ የእግዚአብሔር ልጆች ከማለት ይልቅ “መላእክት” ተብለው ተተርጉመዋል፡፡ በኢዮብ ውስጥ በሚገኙት ምንባቦች፣ ዕብራይስጡ የሚናገረው “ቤናይ ሃኤሎሂም” የቁም ትርጉሙም “የእግዚአብሔር ልጆች” ማለት ነው፡፡ በሌሎች ምንባቦች ግን ተመሳሳይ ቋንቋ እናገኛለን፡፡ የእስራኤልም መንግሥት ራሱ እንደ ዘፀአት ምዕራፍ 4 ቁጥር 22 እና ሆሴዕ ምዕራፍ 11 ቁጥር 1 በመሳሰሉ ክፍሎች ውስጥ የእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ እንደ 2ሳሙኤል ምዕራፍ 7 ቁጥር 14 እና መዝሙር 2 ቁጥር 7 ባሉት ክፍሎች ደግሞ የእስራኤል ሰብዓዊ ነገሥታትም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪው የሰው ዘር አዳምም፣ በሉቃስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 38 ላይ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ሁላችንም ክርስቲያኖች እንደምናውቀው፣ በበርካታ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ አማኞች ልጆቹ ተብለው ተጠርተዋል፡፡ ይህንንም እንደ ማቴዎስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 9 እና 45፣ ሉቃስ ምዕራፍ 20 ቁጥር 36 እና ሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 14 እና 19 በመሳሰሉ ክፍሎች ላይ እንመለከተዋለን፡፡ ጳውሎስም በገላትያ ምዕራፍ 3 ቁጥር 26 እንደጻፈው፡ በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ሮሜ 3፥26) ታዲያ “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለው መጠሪያ በራሱ ለብቻው ኢየሱስ መለኮታዊ ነው የሚለውን ካላረጋገጠ፣ ቤተክርስቲያን ለምን ዋና ጉዳይ አድርጋ ያዘችው? አዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ እንዴት እንደሚናገር ስንመለከት፣ የእግዚአብሔር ልጅነቱ ለየት ባለ መንገድ መሆኑ ግልጥ ይሆንልናል፡፡ በመሠረቱ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከምናገኛቸው ትኩረት ሳቢ ነገሮች ዋነኛው ኢየሱስ ልዩው የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ያም እርሱ የእግዚአብሔር ማንነት 
ተካፋይ የመሆኑ ነገር ነው፡፡ ለየት ባለ መንገድ ስናስቀምጠውም ኢየሱስ ራሱ አምላክ ነው፡፡ እኛ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው በማደጎ (Adoption) በተገኘ ዝምድና እንጂ በማንነት አይደለም:: ኢየሱስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ ነው፡፡ እርሱ ለዘወትር የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ይኖራል፡፡ የኢየሱስ ልዩ ልጅነት በተለይም በዩሐንስ ወንጌል በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ለአብነት ያህል፣ በምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እስከ 18፣ ኢየሱስ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ይነግረናል ፣ ማለትም እርሱ ራሱ እግዚአብሔርም አንድያ የአብ ልጅም ነው ማለት ነው፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 18 እስከ 23 ኢየሱስ እንደ አብ ልጅ፣ ከላይ የመጣ እንጂ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነሲናገርም እንመለከተዋለን፡፡ ደግሞም በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 30 ላይ ኢየሱስ እርሱ እና አብ አንድ መሆናቸውን በተናገርበትም ክፍል ላይ እናገኘዋለን፡፡ ዮሐንስ ነገሩን ይበልጥ ግልጥ ያደረገበት ስፍራ ዮሐንስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 18 ላይ ያለው ነው፡፡ በዚያ ስፍራ የጻፈውን አድምጡ፡ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ (ዮሐንስ 5፥18) ኢየሱስ ስለ ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ሲናገር፣ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል ነኝ ማለቱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ሲናገር፣ እርሱ ልዩና ነው ማለቱ እንደሆነ ክርስቲያኖች የመረዳት መብት አላቸው፡፡ የኢየሱስ መለኮታዊ ልጅነት በተጨማሪም በሌሎች በርካታ የአዲስ ኪዳን ምንባቦችም ተገልጦ እናገኘዋለን፡፡ ይህንንም ጳውሎስ ከትስጉትነቱ በፊት እንኳን ኢየሱስ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ ስለ መሆኑ ባስተማረበት በሮሜ ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 እና 4 ደግሞም በምዕራፍ 8 ቁጥር 3 ላይ እናገኘዋለን፡፡ በዕብራውያን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 1 እስከ 3 እንደ እግዚአብሔር ልጅ፣ ኢየሱስ ፍጥረተ ዓለምን የፈጠረ የአብ አምሳል መሆኑ በተነገረበት ክፍልም እናገኘዋለን፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ቦታዎች፣ ኢየሱስ እንደ እግዚአብሔር ልጅ የተገለጠው ዘላለማዊና መለኮታዊ ማንነቱን በሚገልፅ ለየት ባለ መንገድ ነው፡፡ ኢየሱስ መለኮታዊና ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለው አትኩሮት በትምህርተ ሥላሴ ውስጥ እንዲህ ተገልጧል፡ እግዚአብሔር ሦስት ሰውነት፣ ግን አንድ ማንነት አለው፡፡ አዲስ ኪዳን ኢየሱስ ከስላሴ አንዱ የሆነው፣ እግዚአብሔር ወልድ መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ግን ከእግዚአብሔርና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውስ ግንኙነት ምንድን ነው? ቀደም ብለው በነበሩት ትምህርቶች እንደተነጋገርነው፣ በስላሴ ማንነት ላይ የተደረገው ጥናት የሚያተኩረው በእግዚአብሔር ማንነትና ኅላዌ ላይ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ፣ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በኃይልም ቢሆን በክብር እኩል ነው፡፡ ሦስቱም የእግዚአብሔር አካላት ወልድንም ጨምሮ የማይገደቡ፣ ዘላለማዊና የማይለዋወጡ ናቸው፡፡ ሦስቱም እንደ ጥበብ፣ ኃይል፣ቅድስና፣ ፍትህ፣ መልካምነትና እውነት የመሳሰሉ ተመሳሳይ መሠረታዊ ባሕርያት አሏቸው፡፡ ደግሞ፣ ስለ ስላሴ ያለው ኤኮኖሚያዊ አመለካከት የእግዚአብሔር አካላት አንዳቸው ከሌላቸው ጋር እንዴት እንደሚገናኙ ይገልጥልናል፡፡ ከዚህም አመለካከት፣ እያንዳንዳቸው የተለያዩ ሃላፊነቶች፣ የተለያየ የሥልጣን እርከን እና እንዲያከናውኑ የተሰጣቸው ተግባር መኖሩን እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ፣ ክርስቶስ ዘወትር የእግዚአብሔር ልጅ፣ ለእግዚአብሔርም ሥልጣን ራሱን ያስገዛ ነው፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 38 ኢየሱስ ለአባቱ ያለውን መሰጠት ሲገልጥ የተናገረውን እናዳምጥ፡ ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። (ዮሐ 6፥38) በዮሐንስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 28 እና 29 ተመሳሳይ የሆነውን ነገር መግለጡን እነዚህን ቃላት ስናነብብ እንረዳለን፡ ስለዚህም ኢየሱስ፦ የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም አላቸው። (ዮሐ 8፥28-29) በአዲስ ኪዳን ከዳር እስከዳር ወልድ ለአብ ሥልጣን ራሱን በፈቃዱ አስገዝቶ እናገኘዋለን፡፡ በመካከላቸው ግጭት የለም፣ ምክንያቱም ወልድና አብ ዘወትር ይስማማሉና፡፡ ነገር ግን ከፍ ያለው ሥልጣን የአብ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ፣ በዚሁ የስላሴ ኤኮኖሚ ውስጥ፣ ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ለምሳሌ፣ ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 26 የተናገረውን አድምጡ፡ ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ (ዮሐ 15፥26) በሎችም ምንባቦች፣ እንደ ሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 9 እና 1ጴጥሮስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 11 ባሉት ክፍሎች፣ መንፈስ ቅዱስ “የክርስቶስ መንፈስ” ተብሎ ተጠርቷል እንደገናም መንፈሱ በክርስቶስ የተላከ መሆኑን አመልክቷል፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች ወልድ የስላሴ ሁለተኛ አካል ነው በሚለው ድምዳሜ ተጠቃልለዋል፡፡ እርሱ የስላሴ ማንነት ሁለተኛ አካል ነው፣ ምክንያቱም ከአብ ወጥቶአልና እርሱም ሦስተኛውን አካል መንፈስ ቅዱስን ልኳል፡፡ በኤኮኖሚያዊ ስላሴ ወስጥ ሁለተኛው አካል ነው ምክንያቱም የመሃከለኛውን ስፍራ ይዟልና፡፡ እርሱ ለአብ የሚገዛ ሲሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን ሥልጣን አለው፡፡ በቀደመችው ቤተክርስቲያን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ለሙሉ መለኮት ነው የሚለው የእምነት አቋም በክርስትና እምነት ውስጥ ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን፣ ኢየሱስ በእውነት ፍፁም አምላክ ነው ብሎ ማረጋገጥ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለው ቃል ያለውን ወሳኝነት ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ “ጌታ” የሚለው ስያሜ እንዴት የኢየሱስን መለኮትነት እንደሚያመለክት እንመለከታለን፡፡

Wednesday, July 29, 2015

The truth is that this fallen angel is a “hyper-realistic sculpture”

 http://m.snopes.com/fallen-angel/
FACT CHECK:   Do photographs show a real-life fallen angel that was captured after it dropped from the skies?

image: http://m.snopes.com/wp-content/uploads/2015/07/fallen-angel-top.jpg




Claim:   Photographs show a real-life fallen angel that was captured after it dropped from the skies.
image: http://www.snopes.com/images/m/false.png   FALSE

Example:     [Collected via Tumblr, July 2015]
There is this article on Facebook saying this: BREAKING NEWS: Real Life Fallen Angel Has Fallen From The Sky In London.
Origins:    In July 2015, a series of photographs purportedly showing a fallen angel who dropped from the skies above London began circulating online:
image: http://m.snopes.com/wp-content/uploads/2015/07/fallen-angel-2.jpg



image: http://m.snopes.com/wp-content/uploads/2015/07/fallen-angel-3.jpg



While some web sites correct noted that the photographs depicted an art installation, others decided to use the images to create a fake news story about a “real” fallen angel. The web site Trending Stylist, for example, claimed that the photographs depicted an angel captured in Texas:
A human like “Angel” has fallen out of the skies over Texas. The extremely human like creature with what seems to be “angel” wings as arms appears to have fallen from the sky at around 1:50pm this afternoon.
The ‘Angel’ like creature was quickly rushed away by what seemed to be undercover police officers dressed in suits and sunglasses, resembling the characters in the hit movie Men in Black.
It comes just hours before NASA announced finding ‘Earth 2.0′ the most habitable planet ever discovered.
Zon News shared a nearly identical story that simply changed the setting to London:
A human like “Angel” has fallen out of the skies over London. The extremely human like creature with what seems to be “angel” wings as arms appears to have fallen from the sky at around 1:50pm this afternoon.
The ‘Angel’ like creature was quickly rushed away by what seemed to be undercover police officers dressed in suits and sunglasses, resembling the characters in the hit movie Men in Black.
The truth is that this fallen angel is a “hyper-realistic sculpture” created by Beijing artists Sun Yuan and Peng Yu in 2008:
Sun Yuan & Peng Yu’s works always start with a paradox. Their early objects and installations are made from real cadavers or human fat tissues. Yet, even though playing on the speculative and the spectacular, they focus on the investigation of the paradox rather than merely exploiting the spectacular. The tension between the bodies, organic tissues or animals and their artistic manifestations corresponds to the transposition of subjects from the plane of immanence onto the plane of transcendence. In their recent installations using hyper-realistic sculpture, they reverse their original practice: imagination and mythological subjects penetrate into the realm of everyday life and reality. Angel, a life-size sculpture in fiber-reinforced polymer and silica gel of a fallen angel is typical of this new approach. The angel, an old woman in a white gown and with featherless wings, is lying face-down on the ground; maybe sleeping, maybe dead, but certainly immobile and frozen into an all too realistic image. The supernatural being, now nothing more than an impotent creature, can neither carry out any supreme will nor be of any help to those believing in its existence. The angel is true but ineffective; dreams and hopes are sincere yet vain.
image: http://m.snopes.com/wp-content/uploads/2015/07/fallen-angel.jpg



Read more at http://m.snopes.com/fallen-angel/#GjcdFtDm0CteTkDg.99

Sunday, July 26, 2015

ሐዋርያቱ ደቀመዛሙርት እንጂ ሐይማኖተኞች አልነበሩም


የጌታ ኢየሱስ ሐዋርያት ጴንጤም፣ ኦርቶዶክስም፣ካቶሊክም አልነበሩም፡፡ እነርሱ ጌታን በፍጹም አምላክነቱ እና ሰውነቱ ተረድተውት መዳን በእርሱ ብቻ እነደሆነ ሰብከውና አስተምረው ያለፉ ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡ በውስብስብ የስነመለኮት ጥያቄዎች ውስጥ እራሳቸውን ዘፍቀው ሲፈላሰፉ እና ሲከራከሩ የኖሩ አይደሉም፡፡ በወቅቱ ለተነሱ የስነመለኮት ጥያቄዎች እና የኑፋቄ ትምህርቶች እንደቃሉ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ያለፈ ነገር ውስጥ አልገቡም፡፡
ከእነርሱ በኋላ ጥቂት መቶ አመታት ቆይቶ በተነሱ አባቶቸ ዘመን ነው የስነመለኮት ውስብስብ ፍልስፍናዎችና ክርክር ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል የዳረጓት፡፡ በ5ኛው ክ/ዘ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወደ ኦርቶዶክስነትና ካቶሊክነት ያመራው ጭቅጭቅ ከረረ፡፡ በ16ኛው ክ/ዘ ደግሞ ፕሮቴስታንት ከካቶሊክ ወጣ፡፡ ከዚያ በኋላ እስከአሁን ባለው ዘመን ደግሞ የፕሮቴስታንት መበጣጠቅ ቀጠለ፡፡እንዳውም ሲበጣጠቁ አሁን አሁን «እግዚአብሔር ተናገረኝ፣ራዕይ ሰጠኝ»በሚል ሽፋን ነው፡፡
ይህ አይነቱ እግዚአብሔር ፣ ቃሉን የሚፃረር እግዚአብሔር፣ እርሱ ልበወለድ አምላክ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ግን፣ እርሱ ቃሉን የሚያከብር፣ ሐዋርያቱን በአንድነት ያኖረ ፣ የአንድነት አምላክ ነው፡፡
ሐዋርያቱ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ በ451 ዓ.ም /በእኛ አቆጣጠር/ በኪልቄዶን ጉባኤ በተከሰሰው ያለመግባባት የእስክንድሪያ /የግብጽ/ የእምነት አባቶች ከሮም የእምነት አባቶች ሲለያዩ እና ኦርቶዶክስና ካቶሊክ የሚሉ ቃላት የተከፋፈሉ ቤተእምነቶችን በመወከል በመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ በ1054 /እ.ኤ.አ/ የምስራቅ ኦርቶዶክስ ከሮም ካቶሊክ ሊለያዩ፣ ኦክቶበር 31፣1517 ሉተር 95 የልዩነት ነጥቦችን በዊትንበርግ ባለችው ቤተክርስቲያን በር ላይ ለጥፎ ከካቶሊክ ሲወጣ እና ለጴንጤነት መሰረት ሲጥል፣ከዚያ በኋላ ደግሞ ብዙ ቤተእምነቶችና /የእምነት ክፍሎች / Sects / በጥቃቅን ልዩነቶች ጴንጤነትን ሲበጣጥቁት፣ የየቱ አባል ይሆኑ ነበር ብላችሁ ታስባላችሁ?
ለእነርሱ ሁሌም ትክክለኛ መንገድ ኢየሱስ ፣መጽሐፍ ቅዱስና የደቀመዛሙርት አንድነተ ነው፡፡ ትክክል ያልሆነውን ትምህርት በትክክለኛው ያፈርሳሉ፣ ኑፋቄንያወግዛሉ፡፡ ግን ትክክል የሆነውም ደቀመዝሙር ሆኖ ደቀመዛሙርትን ለክርስቶስ እንዲያፈራ መንገድ ያሳዩታል እንጂ አንተ በያዝከው አንጃ ተከታዮችን እያፈራህ ቀጥል አይሉትም፡፡ ምክንያቱም «እኔ የጳውሎስ፣ እኔ የኬፉ፣ እኔ የአጰሎስ፣ እኔ ደግሞ የክርስቶስ » የሚል የአንጀኝነት አካሄድ አልተፈቀደምና ነው፡፡
እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው ከስነመለኮትና ስነአመራር ውስብስብ ቀመር ይልቅ ደቀመዝሙር ብቻ ሆነን የክርስቶስን የህይወት ምሳሌ እንድንተገብር እያሳዩን ያሳርፉን ነበር፡፡
ለምሳሌ ሙሉ ወንጌል ከሙሉ ወንጌል/፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አብያተ እምነት /ዲኖሚኔሽኖች/ አመራር፣ ላይ ላዩን እንጂ ፍጹም አንድነት ፍጹም የማይታሰብ ነው፡፡ አዳዲስ ከሚፈለፈሉትማ ጋር ጠቡ እና ሽኩቻው የከረረ ነው፡፡
አንድ ጴንጤ እሁድ አጠገቡ ያለውን የእርሱ ያልሆነ ቤተእምነተ አልፎ የእኔ ወደሚለው ለመሄድ በታክሲም በእግርም ስንት ርቀት አቆራርጦ በመሄድ ያመልካል፡፡ የአጥቢያ አመለካከት በኦርቶዶክስ እንኩዋ እንዲህ አይደለም፣ ሁሉም በሚቀርበው ደብር ነውና የሚሰበሰበው ልዩ ፕሮግራም ካልሆነ በቀር፡፡ አንዱ ለፍቶ ያስተማረውን ሌላው የጴንጤ «ቤተክርስቲያን»ከወሰደ ቅሬታ ይፈጠራል፣ከተደጋገመ ከማስኮብለል ይቆጠራል፣ ከጨመረ ግን በነፍሳት ዘረፋ ይከሰሳል፣«ዘራፊው» የአብያተ ክርስቲያናት ህብረት አባል ከሆነ፡፡
እና ሐዋርያቱ የዚህ አይነት እቃእቃ ጨዋታ አካል ይሆኑ ይመስላችኋል?
እነርሱ ጴንጤም፣ካቶሊክም፣ ኦርቶዶክስም አልነበሩም፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ አንድነትዋን ጠብቃ በኖረች ኤክሌሺያ እንጂ አባልነታቸው በድርጅት ውስጥ አልነበረም፡፡

Disciples of Jesus/Restoration

1bible.page.tl 

አሳሳች ድንቅና ተአምራት


ሰው በባህሪው ከአማልክት ልዕለ ተፈጥሮአዊ ምልክቶች ማየትይፈልጋል፡፡ እስራኤላውያን ጌታን ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ይጠይቁት እንደነበር መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡«መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ» ይላል 1ቆሮ 1፡22፡፡
እውነተኛ ድንቅና ተአምራት የመኖራቸውን ያህል ተመሳስለው የሚሰሩ መኖራቸውን ካላወቅን ተሳስተን ማለቃችን ነው፡፡ እነዚህም፡-
1. ከእግዚአብሄር ለፈተና እና ለፍርድ የሚላኩ ዘዳ 13፡1-4እነዚህ ነቢያት በብሉይ ኪዳን ዘመን ድንቅና ተአምራትን እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ግን ከቃሉ ባፈነገጠ መንገድ የሚሰሩ መሆናቸውን መርምሮ መቀበልና መጣል ለህዝቡ የተተወ ነው፡፡ ምክንያቱም ነብያቱ ሌሎችን አማልክት ለማምለክ ህዝቡን ያነሳሱ ነበርና እነሱን መከተል ያለመከተሉ እግዚአብሄርን የመውደድም ሆነ ያለመውደዱ መፈተኛ ነበርና ነው፡፡
በአዲስ ኪዳን የምንሰግድለት ተቀርፆ የተሰራ ጣኦት የለም፡፡ ግን ገንዘብና ሆድ ጌታ ሊሆኑ እንደሚችሉ በግልጥ ተነገሮናል፡፡ ከኢየሱስ በላይ የቤተክርስቲያናችንን ወይም የልባችንን መድረክ የገዛ ነገር እርሱ ጣኦታችን ነው፡፡ ለምሳሌ የብልፅግና ወንጌል ሰባኪያን መድረክ ከኢየሱስ በላይ በገንዘብና ጤና ስኬት ስብከት ተይዞአል፡፡ ስለዚህ ምድራዊ ስኬት በብልጽግና ወንጌል ወይም የእምነት ቃል ሰባኪያን ዘንድ ጣኦት ነው፡፡ እንግዲህ እዚያ ስፍራ ባሉ ነቢያትና ፓስተሮች ምንም ያህል ድንቅና ተአምራት ቢሰራ ልንታለል አይገባም፡፡ ልንቀበላቸውም አይገባንም፡፡ ገንዘብ ጣኦታቸው ነውና፡፡
ምክንያቱም የድንቅና ተአምራቱ ምንጭ ሰይጣን ነው፡፡ በተለይ በመጨረሻው ዘመን እውነት የሆነውን የእግዚአብሄር ቃል የሚገፋ ትውልድ ለዚህ ፍርድ ተጋልጦ እንዲሰጥ እና እንዲታለል የሚፈቅድ ራሱ እግዚአብሄር ነው፡፡ «በዚህም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፣ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ የገለጣል፣ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉ እና በምልክቶች በሀሰተኞች ድንቆችም በአመፅም መታለል ሁሉ እንደሰይጣን አሰራር ነው፡፡
ስለዚህም ምክንያት፣ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በአመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፣ ሀሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሄር የስህተትን አሰራር ይልክባቸዋል» 2 ተስ 2፡8-12፡፡
ስለ አክአብና ስለ ነቢያቱ፡- «መንፈስም ወጣ በእግዚአብሄርም ፊት ቆሞ፡- እኔ አሳስተዋለሁ አለ፡፡ እግዚአብሄርም ፡- በምን? አለው፤ እርሱም፡- ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሀሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ፡፡ እግዚአብሄርም፡-ማሳሳትስ ታሳስተወለህ ይሆንልሃልም ውጣ፣ እንዲሁም አድርግ አለ፡፡ አሁንም እነሆ፣ እግዚአብሄር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሀሰተኛ መንፈስ አድርጎአል…» የተባለው ምንድነው? በንጉሱ በአክአብ ላይ ለፍርድ የወጣ አሳሳች መንፈስ /ሰይጣን/ ነቢያቱን መቆጣጠሩን ከዚህ ከ1ነገ 22፡21-23 እንረዳለን፡፡ ሰይጣን በበሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሄር ፊት ቀርቦ ይነጋገር እንደነበር ከመጽሀፈ ኢዮብ እንረዳለን፡፡ ስለ ሳኦልም፡- «የእግዚአብሄርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፣ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሄር ዘንድ አሰቃየው» የሚለው እንዲሁ ሳኦል በአመፅ ለሰይጣን ተላልፎ መሰጠቱን የሚያሳይ ፍርድ ነው 1ሳሙ 16፡14፡፡
ዛሬ ለዚህ ስህተት አሰራር የተጋለጡ አብያተ እምነቶች በኢትዮዽያ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት እና ቪዥነሪ አብያተክርስቲያናት ህብረት ውስጥ በአባልነት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ በሳተላይት ዲሽም የምንከታተላቸውን ፕሮግራሞች ከዚህ አንፃር እያጣራን መቀበል ይገባናል፡፡ የዘወትር ስብከታቸው ኢየሱስ ሳይሆን የሀብትና የጤና ስኬት የሆነ ነቢያትና ፓስተሮች ድንቅና ተአምራት ሲሰሩ ብናይ መንፈሳችንን መጠበቅ ይገባናል፡፡
1. 2. የበግ ለምድ በለበሱ ነቢያት የሚሰሩ ድንቅና ተአምራት
ማቴ 7፡15-23 እነዚህ ነቢያት ተኩላዎች ናቸው፣ የበግ ለምድ ለብሰው ከበጎች ተቀላቅለዋል፡፡ አላማቸው በጎችን መብላት ነው፡፡ ክፉ ፍሬ በሚያበቅሉ ክፉ ዛፎች ተመስለዋል፡፡ መልካም ፍሬ የላቸውም፡
ግን ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ ይላሉ፣ የእግዚአብሄርን ፍቃድ ግን አያደርጉም፡፡ ኢየሱስን ይሰብካሉ ግን ዓመፀኞች ናቸው፡፡ ገንዘብ ሀብትና ዝና ነው አላማቸው፡፡ በጌታ ስም ትንቢት ይናገራሉ፣ አጋንንትን ያወጣሉ፣ ድንቅና ተአምራትም ያደርጋሉ፡፡ ግን በጌታ የታወቁ/የዳኑ/አይደሉም፡፡ጌታም ድንቅና ተአምራት ስለማድረጋቸው አልተከራከራቸውም፡፡ የነገራቸው በእርሱ ያልታወቁ እና አመጸኞች መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡
ከዚህ የምንረዳው ሰይጣን አስመስሎ በመቀባት ነቢያትና ፓስተሮችን ሊያስነሳ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ድንቅና ተአምራቱ የእርሱ መሆናቸው እንዳይነቃ የጌታን ስም እንዲጠሩ ያደርጋል፡፡ እነዚህ በስንዴው ማሳ መካከል ዲያብሎስ የዘራቸው እንክርዳዶች ናቸው፡፡ ፍሬ እስኪያወጣ ድረስ ስንዴው ከእንክርዳዱ እንደማይለይ ሁሉ እነዚህን ነቢያት ከእውነቶቹ መለየት ያዳግታል፡፡
ለመንቀል እንኩዋ ሙከራ ቢደረግ ስንዴውን በስህተት አብሮ የመንቀል ስህተት ሊሰራ ስለሚችል እስከመከር ጊዜ /መጨረሻው ዘመን/ አብረው እንዲቀጥሉ ተፈቅዶአል /ማቴ 13፡ 24-30፣ 36-43/፡፡ ድንቅና ተአምራት በበዛባት የቆሮንጦስ ቤተክርስቲያን መካከል ሰይጣን እንደዚህ አይነት ሀዋርያትን አስርጎ አስገብቶ ነበር፡፡ «እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሀዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፣ ውሸተኞች ሀዋርያትና ተንኮለኛ ሰራተኞች ናቸውና፡፡ ይህም ድንቅ አይደለም፡ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልዓክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም …» 2ቆሮ 11፡13-15፡፡ እነዚህ ሐዋርያ ተብዬዎች ጳውሎስን ተቀባይነት እስኪያሰጡት ድረስ ዋነኛ ሐዋርያት ተብለው በቤተክርስቲያኒቱ ስፍራ አግኝተው ነበር፡፡
ጌታ የድንቅና ተአምራት አምላክ ነው፣ እውነተኛ ድንቅና ተአምራት ዛሬም አሉ፡፡ እውነተኛ ነቢያትም አሉ፡፡ ነገር ግን በዚያው መጠን ለፍርድና ለፈተና የተላኩ እና ሰይጣን አመሳስሎ እነርሱ እንኩዋን ሳያውቁት የሚጠቀምባቸው አገልጋዮች የብልፅግና ወንጌልን ስህተት ሰተት አድርገው በመካከላችን አስገብተው ድንቅና ተአምራት የሚሰሩ አሉ፡፡ ስራቸው ክፉ መሆኑን እያወቅናቸው /ዝሙት እየሰሩ፣ ገንዘብ ከቤተክርስቲያን እያጭበረበሩ ፣ መለያየትን እየዘሩ እና ቤተክርስቲያን እየከፈሉ/ ድንቅና ተአምራት የሚከተላቸው አሉ፡፡
«ጌታ ለህዝቡ ሲል እየተጠቀመባቸው ነው» የሚለውን የየዋህነት አካሄድ ትተን ብንመረምራቸው መልካም ነው፡፡ የድንቅና ተአምራቱ ምንጭ ሰይጣን ነው፡፡ የምንመረምራቸው ደግሞ ፡-
ሀ. በቃሉ
ለ. መናፍስትን በመለየት የፀጋ ስጦታ
ሐ. መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ስለሚመረምር መንፈሳዊ
ክርስቲያን በመሆን
መ. በፍሬአቸው
ሠ. የመገለጡ /ድንቅና ተአምራቱ/ ክብር ለኢየሱስ መሆኑን በማረጋገጥ ሊሆን ይችላል፡፡
ክብር ሁሉ ለነገስታት ንጉስ ለጌታ ኢየሱስ ይሁን!


ጴንጤ Vs አይሁድ


ኢየሱስም ወደ ፊሊጶስ ቂሳሪያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎቹም ኤልያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት’’ ማቴ 16፡13-14፡፡
በአብዛኛው ሀዋርያት ከህዝቡ ያገኙት መረጃ የኢየሱስን ማንነት በአንድ የብሉይ ኪዳን ነቢይ ደረጃ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ለእነርሱ ጌታ ከአንድ የብሉይ ነቢይ የበለጠ ምንም አላደረገም፡፡ እንደውም ኤሊያስ ዝናብና እሳትን ለምኖ ከሰማይ ምልክት አሳይቶአል፡፡ ሙሴ ከሰማይ መና፡ ሳሙኤልም እንዲሁ ነጎድጓድና ዝናብ እንዲወርድ አድርገዋል፡፡
ጌታ ደቀመዛሙርቱን ህዝቡ ስለእርሱ ማንነት ያለውን ግንዛቤ በተመለከተ ጥያቄ እንዲጠይቅ ያደረገው በዚያው ማቴ 16፡1 ላይ ከፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው’’ የቀረበለት ልመና ነው፡፡ ከሰማይ ምልክት ካሳያቸው ከነሙሴ፣ ሳሙኤል፣ ኤልያስ ወዘተ… ጋር እኩል ሊያደርጉት፡፡
ሐዋርያቱ ጭምር ስለ ሰማሪያ ሰዎቸ ፡-‹ ጌታ ሆይ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? › ብለውት ነበር ሉቃ 9፡54፡፡ ይህ የኤልያስ አገልግሎት በሐዋርያቱ ላይ ጭምር ተፅዕኖ አሳድሮአል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ጌታ እንዚህን ሰዎቸ / ያዕቆብን፣ ዮሐንስንና ጴጥሮስን/ ይዞ ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው፡፡ በፊታቸውም በመለወጥ ታላቅ ክብሩን አሳያቸው፡፡ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ በጌታና በነሱ ክብር መካከል ምን ያህል ልዩነት እንዳለ ማስተዋል ነበረባቸው፣ ከመጭበርበር ይድኑ ዘንድ ማቴ 19፣1-8፡፡ ከዚያ ሲመለሱ የጠየቁት ጥያቄ ከነበረባቸው ጥያቄ ማረፋቸውን ያሳያል፡፡«እንግዲህ ፃፎች ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለምን ይላሉ?» ማቴ 17፡10፡፡ ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል በ1ቆሮ 1፡22 ላይ «መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ» የሚለው፡፡ ይህ ምልክት ናፋቂነት ከዳኑም በኋላ በብርቱ በጴንጤዎች ዘንድ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ምልክት ያላመኑትን ወደ ጌታ ይስባል እውነት ነው፡፡ ጌታም በድንቅና ተአምራት የሐዋርያቱን ምስክርነት እውነትነት ያጸና ነበር፡፡ ታላቅ ስህተት የምንሳሳተው የጌታን ድንቅና ተአምራት ለትልቅነቱ መመዘኛ አድርገን የወሰድነው እንደሆነ ነው፡፡ምክንያቱም አዲስ ኪዳን ደግሞ ደጋግሞ እንደሚነግረን የሚታየውና የማይታየው ዓለም ሁሉ የተፈጠረው በእርሱ መሆኑን ነውና፡፡
ይህንን ትልቅ አምላክ በአይምሮ ሊገመት የማይችል ኃይል ባለቤት አንድ አይን ሲፈውስ፣ሽባ ሲተረትር፣ ኩላሊት ሲፈውስ ወዘተ አይቶ እና አሳይቶ ትልቅነቱን ለማወጅ መነሳት ትልቅ የመረዳት ችግር ነው፡፡ እርሱን ከብሉይ ዘመን ነቢያት ጋር ማጭበርበር ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ከሐሰተኛው ክርስቶስ ኃይል ጋርም ማምታታት ይሆናል፡፡
አጋንንት በስሙ ቢወጡ ለትልቅነቱ ማስረጃ አይሆንም፣ ነገር ግን ለሰው ልጆች ስላሳየው ምህረት ምልክቶች ናቸው፡፡ ደስታችንም አጋንንት በስሙ ስለተገዙልን ሳይሆን ምህረት ተደርጎልን በሰማያት ስማችን በመጻፉ ሊሆን እንደሚገባ ጌታ ራሱ ተናግሮአል ሉቃ 10፡20፡፡
ዮሐ 4 ላይ የተጠቀሰችው ሳምራዊት ሴት ጌታን፡-1. እንደ ተራ አይሁዳዊ ማለትም
መንገድ ሲሄድ የደከመው፣ ውሃ የጠማው፣ ከዚያ መቅጃ ስለሌለው ሊቀዳ የሚመጣ ሰው የሚጠብቅ አድርጋ ተረድታዋለች / ቁ. 9-11/፡፡ የገዛ አገሩ ሰዎችም፡-«ይህን ጥበብና ተአምራት ከወዴት አገኘው የጸራቢ ልጅ አይደለምን» እያሉ እንዲሁ ይረዱት ነበር ማቴ 13፡54፡፡
2. እንደ ነብይም ተረዳችው /ቁ.19/
ሌሎችም ፤- ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ፤ «ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ» ዮሐ 6፡14 ፡፡ ተከታዮቹም «በስራና በቃል ብርቱ ነብይ» ሲሉ ተናግረውለታል ሉቃ 24፡19፡፡
3. በመጨረሻም በመሲህነት ተረዳቸው /ቁ. 25/
ጴጥሮስም፡-« አንተ ክርስቶስ….ነህ» ብሎታል ማቴ 16፡16 ላይ፡፡ ለቆርኔሌዎስ ሲሰብክም እንዲሁ ፡- « እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፣ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ …. በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአትን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል» ብሎአል ሐዋ. 10፡38፣43፡፡
የብዙ አይሁዳውያን መረዳት ጌታ ተራ አይሁዳዊ ነብይ በመሆኑ ላይ የተገደበ ነው፡፡ ጥቂቶች ደግሞ መሲህነቱን ተቀብለዋል፡፡ እጅግ በጣም ጥቂቶች ደግሞ የእርሱን ማንነት ማለትም ፍፁም አምላክነቱን ተረድተዋል፡፡
4. ጥቂቶች ፍጹም አምላክ እንደሆነ ተረዱ /ዮሐ 20፡28/:
ዮሐ. 1፡1-3፣ ሮሜ 9፡5 ቲቶ 2፡13፣ 2 ጴጥ 1፡1፤1ዮሐ 5፡20
‹እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ህይወት ነው › ይላል፡፡ ዓለማት
ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋል / ዕብ 1፡2/፡፡
ማጠቃለያ
አይሁዳውያን ለጌታ ታላቅነት ማስረጃ ለዚያውም ገና ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ጋር የእኩያነት ደረጃ ሊያጎናጽፉት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይጠይቁ ነበር፡፡ ጴንጤ ጋር ያለው ችግር ደግሞ የሚመነጨው ጌታ በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ተቀብቶ ያደረገውን ድንቅና ተአምራት ሲያሳድዱ ሳያውቁት አምላክነቱን መዘንጋታቸው ነው፡፡ አንድ አጋንንት በስንት እዝጊዎታ ሲጮህ “ጌታ ትልቅ ነው” ተብሎ እልልታውና ጭብጨባው ይቀልጣል፡፡ አንድ በሽተኛ ሲፈወስ ሰፈር በጩኸት ያናጋል፡፡ በመገለጥ የአንድ ሰው ስም የተጠራ እና አሁን እየሆነ እንዳለው ስልክ ቁጥሩ የተነገረ እንደሆነ አገር በእልልታ ይቀልጣል፡፡በየአውሊያው ቤት ይህ እኮ ቀላል ነገር ነው፡፡ ለመሆኑ የሚታየውንና የማታየውን አለም የፈጠረ ማነው?
ደስታው ጥሩ ፣ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ግን ስለተደረገልን ምህረት እንጂ ስለጌታ ትልቅነት ከሆነ ስህተት ነው፡፡ “ለምን?” ሲባል ጌታ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ፣ ባለቤትና ገዢ ስለሆነ በዚህች ትንሽ ምልክት ትልቅነቱ አይመዘንምና ፡፡ ስለዚህ የጌታን ማንነት በሚዛናዊነት ተረድቶ ተሀድሶን ከምልክቶችና ከተአምራቶች ጋር ብቻ በማያያዝ መሞቁና መቀዝቀዙ ቢቀር ለማለት ነው፡፡

1bible.page.tl 

ብሉይ ኪዳናዊ ጴንጤነትና ወጥመዱ



የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን (የኢትዮጵያዋን ማለቴ ነው) በብሉይ ኪዳን የታቦት ሥርዓትዋ ስትተች የኖረች የፕሮቴስታንት እምነት በተራዋ በብሉይ ኪዳን አስተምህሮዎች ተተብትባለች፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ለህዝብ በሚስማማ መልክ ተቀምሮ ይቀርባል፡፡
አዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ሲበረዝ ለብዙዎች ስሜት ተስማሚ ሆኖ ስለተገኘ ለመቃወም ጉልበት ጠፋ፤ አሮጌው ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ከሰመረ ምድራዊውን ብልጽግና እና ስኬት እንደሚያንበሸብሽ የታወቀ ነው፡፡ ጤና ፣ ቤተሰብ፣ እርሻ፣ በረት ይባረካል፣ ጠላት ይገዛል ወዘተ….፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ካልሰመረ ደግሞ መርገም አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህ የአሮጌው የእስራኤል ኪዳን አሰራር ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ብዙው በምድራዊ ትሩፋት ላይ ያተኮረ ሆኖ እስራኤልን እስካሁን አዲሱን ኪዳን እንኩዋ ሳትቀበል በብልጽናና በመፈራት እያኖራት ይገኛል፡፡ በአባቶች መታዘዝ የዛሬው ትውልድ ይኸው በሞገስ ይኖራል፡፡
ጌታ ኢየሱስም ዓላማው ይህን ለምድር ማዳረስ ቢሆን ኖሮ መምጣትና በመስቀል መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ምድራዊ ብልጽግናና ስኬትን በነዚያው የእስራኤል ነቢያት በኩል ለምድር በኤክስቴንሽን መልክ ማስፋፋት ይችል ነበር፡፡ ብሉይ ኪዳን ከምድራዊ ብልጽግናና ስኬት አንጻር ምንም አልጎደለው፡፡ ስለዚህ እርሱኑ ወደ ምድር ሁሉ ማስፋፋት ይበቃ ነበር፡፡ ጠንክሮ መስራትም ሌላው መፍትሄ ነው፡፡
ቻይና ይህ ፅሑፍ እስከ ተጻፈበት ድረስ በመንግስት ደረጃ ወንጌልን እያሳደደችና እየገፋች ነው፣ ግን የዓለምን ኢኮኖሚ በሁለተኝነት እየመራች ትገኛለች፡፡ በሶስተኛነት የምትከተለዋ ጃፓንም ያለወንጌል በልጽጋለች፡፡ ጣኦት እያመለኩ እንኳ ጠንክረው ሰርተው በልጽገዋል፡፡ ህንድንም እንዲሁ ለቁጥር የሚያታክቱ ጣኦቶች ባለቤት ሆና ሳለች እየበለጸገች ነው፡፡
ነገር ግን የሰው ልጅ የጎደለው መንፈሳዊ ብልጽግና ነበር፡፡ ሌባ በማይሰርቀው፣ ብል በማይበላው በሰማይ የሆነ መዝገብ (ሀብት) ይጎድለው ነበር፡፡ ለዚህ ነው ጌታ መንግስተ ሰማያትን የሰበከው፡፡ አዲስ ኪዳን ወደ ሰማይ ያተኩራል፣ ወደ መንፈሳዊው የእግዚአብሔር ዓለም ብልጽግና፡፡
በሁለቱ ኪዳኖች መካከል መምታታትና መሳከር በፕሮቴስታንት አብያተ እምነት ውስጥ በእጅጉ ጎልቶ እየታየ መጥቶአል፡፡ አዲስ ኪዳናዊ ጸጋ ስጦታዎችን የብሉይ ኪዳን ተስፋዎችን ለማስተማር በተሳሳተ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ሰው ጌታ ኢየሱስን ሲከተልና በህይወቱ እየመሰለው ለመሄድ ሲጨክን መከራና ስደት እንደሚገጥመው አዲስ ኪዳን ቀልጭ አድርጎ አስቀምጦታል ማቴ 5፡11-12፤ ሉቃ 14፡27 ፤ ዮሐ 16፡33፤ 2ጢሞ 10፡12፡፡
ይህንን በዘመናዊው የፕሮቴስታንት ሐይማኖት ውስጥ መስበክ ግን ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ሆኖአል፡፡ ዘዳግም 28 ላይ የተገለጹትን የመታዘዝ በረከት ዝርዝሮች በመድረክ ላይ በመጮህ የአዲስ ኪዳኑ እውነት እንዲጣፋና አደብ እንዲገዛ ይደረጋል፡፡ የጌታን ደም በምድራዊ ብልጽግናና ስኬት መመንዘር እንዴት ያለ ትልቅ መሳት ነው! የአፍሪካዎቹን ጥቂት መልቲ ሚሊየነር የጸጋ ነጋዴ ፓስተሮች ተከትሎ አብሮ ገደል ለመግባት መራወጥ አይገባም፡፡ እውር እውርን ቢመራው ሁለቱም ተያይዘው በገደል እንደሚወድቁ ጌታ ስለ ፈሪሳውያን እና ተከታዮቻቸው ከተናገረው መማር ይገባናል ማቴ 15፡14 ፡፡ ድንቅና ተአምራት አደናግሮን ከሆነ ሰይጣን እንኩዋን ድነው ወደ ገንዘብ ባርነት ለገቡ አገልጋዮች ይቅርና፣ ባልዳኑ ሐሰተኛ ነብያት ተጠቅሞ በጌታ ሥም ብዙ ሊሠራ እንደሚችል ከማቴ. 7 ፡ 15-23 መረዳት አይከብድም፡፡
የሚያሳዝነው ህዝቡም በድንጋያማው መሬት ላይ እንደ ተዘራው ዘር ከመከራና ስደት ነጻ የሚያደርገውን ስብከትና ትምህርት ሲያሳድድ፣ በእሾህ መካከል እንደ ተዘራ ዘር ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያለ ፍሬ እየቀረ ነው (ማቴ 3፡20-22)፡፡ ጌታ ኢየሱስንና መስቀሉን የሚመለከትበት የውስጥ አይኑ በዚህ ተጋርዶአል፡፡
“እንግዲህ ይህን የመሰለ ተስፋ ፣ ስላለን ፣ በድፍረት እንናገራለን፡፡ እስራኤላዊያን የፊቱ መንፀባረቅ እየጠፋ ሲሄድ መጨረሻውን እንዳይመለከቱ ፣ ፊቱን በጨርቅ እንደሸፈነው እንደ ሙሴ አይደለንም፡፡ ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተነበበ ቁጥር ያ መሸፈኛ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልተወገደ ልቡናቸው እንደደነዘዘ ነው፣ መሸፈኛው አሁንም አልተወገደም፣ የሚወገደው በክርስቶስ ብቻ ነውና፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ የሙሴ መጽሐፍት በተነበቡ ቁጥር መሸፈኛው ልቡናቸውን ይሸፍናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል” 2ቆሮ 3፡12-16፡፡ ስለ መዳን ቢሆንም፣ መጽሐፍ የሚለን የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች ላይ ብቻ መንተራስ ያሳውራል፣ መንፈሳዊ ድንዛዜ ያስከትላል ነው፡፡
ከብሉይ ኪዳን እንማራለን፣ እንሰበካለን፡፡ ምክንያቱም የእግዜአብሔር ቃል ነውና ዛሬም ወደፊትም ጥንትም እንደሰራው ይሰራል፡፡ ግን ከአዲስ ኪዳን ተስፋዎችና መርሆዎች ጋር ሳይቃረን መሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ብሉይ ኪዳን የተቀቡ የእግዚአብሔር ሰዎችንም ያልቅ ነበር ዘፍ 12፡2 ፤ መዝ 89፡19-37፡፡ አዲስ ኪዳን ግን ክብርን ለኢየሱስ ብቻ ይሰጣል፡፡ የዘመኑ አገልጋዮች የክብር እና የዝና ሽሚያ ይህን ያገናዘበ አይደለም ዮሐ 3፡30፡፡
ሲጠቃለል ዘዳግም 28 ለእስራኤል የተሰጠ የተስፋ ቃል ነው፡፡ በአሮጌው ኪዳን መሠረት ውል ተጋቢዎቹ እግዚአብሔርና እስራኤል ቃል ኪዳን ሲቋጥሩ የተፈራረሙበት ሰነድ ነው፡፡ አዲስ ኪዳን ግን በቤተክርስቲያንና በእግዚአብሔር መካከል በጌታ ደም አማካኝነት የተቋጠረ ውል ነው፡፡ ስለዚህ የሁለቱን ኪዳኖች የተስፋ ቃሎች ማደባለቅ አይቻልም፡፡
ጌታ፡- “ ንሰሐ ግቡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ” እያለ የሰማይ መንግስትን ሰበከ (ማቴ 4፡17)፡፡ የሰይጣን ቋንቋ ደግሞ አንድ ነው፡- “ የዓለምን መንግስት ከነክብራቸው አሳየውና ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ አሰጥሃለሁ” አለው የሚል ነው ማቴ. 4 ፡ 8-9 ( የአጽንኦት መስመር የእኔ ነው) ፡፡ ምርጫችን ወይ የዓለም መንግስት ወይም የሰማይ መንግስት ይሁን ፡፡ ሁለት ወዶ አይሆንምና ብሉይ ኪዳንን አስታኮ ከመጣብን ስውር የሰይጣን ወጥመድ ማምለጡ ይበጀናል፡፡
Disciples of Jesus/Restoration

1bible.page.tl  

መንፈሳዊ መታለል በነቢያት በኩል


የእግዚአብሔር ህዝብ በነቢያትበኩል ለዘመናት ሲታለል ኖሮአል፡፡ እውነተኛነቢያት እንዳሉ የሳቱ ነቢያትም አሉ፡፡
ነቢያት ከቀናው መንገድ ወጥተው ወደ ስህተት ሲገቡ ህዝብንም ያስታሉ፡፡ በዘመናት መካከል የሰዎችን ልብ ገዝቶ የመያዝ አቅም ከነበራቸው መሪዎች ውስጥ ነቢያት በስህተትም ይሁን በቀና መንገድ ግንባር ቀደም ናቸው ቢባል እብለት አይሆንም፡፡በተለይም በዚህ ረገድ ሐሰተኛ ነቢያት ስኬታማ ነበሩ፣ዛሬም ናቸው (ሉቃ 6፡26)፡፡ በነቢያት በኩልም ሆነ እንዲሁ የእግዚአብሔር ቃል ዕውቀት በነበራቸው ሰዎች ዙሪያ የተከሰተውን መንፈሳዊ/ሰይጣናዊ መታለል በተመለከተ ከመፅሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ምሳሌዎች በአስተዋፅኦ መልክ እንመለከታለን፡፡
ሀ/ ኤልፋዝ
ሰይጣን ኢዮብን በሚስቱ ሳይቀር ፈትኖ ሳይሳካለት በጓደኞቹ በኩል መጣ፡፡ ኤልፋዝ ከእነርሱ አንዱ ነው፡፡መንፈሳዊ በሚመስል ምክር ኢዮብ በኃጢአቱ ምክንያት ይህ ሁሉ እንደደረሰበት ያምን ዘንድ ይዘበዝበዋል ኢዮ 4፡7-9፤5፡17 በተለይ ኢዮ 5፡27፡፡
ይህ መልዕክት ከመንፈሳዊው ዓለም ለኤልፋዝ መጥቶለታል ኢዮ4፡12-21፤ በመጨረሻ ለዚህ አገልግሎቱ ንስሐ ይገባ ዘንድ በእግዚአብሔር ተገስጾአል ኢዮ 42፡7-9፡፡ ልብ ማለት የሚገባን ይህ ሰው ምክሩን የተቀበለው ከሰይጣን መሆኑን ነው፡፡
ለ/ የሚካ ቤት ሌዋዊ
መሳ18፡5-6
ከአገልግሎት ኮብልሎ ጣኦት እያገለገለ ነው መሳ 17፤የአህዛብ አማልክት (ጣኦታት) ደግሞ አጋንንት ናቸው፡፡
ግን ለዳን ነገድ ሰዎች የተፈፀመ መልዕክት አምጥቶአል፣ በእግዚአብሔር ስም፡፡
አህዛብ ለተለየ ጉዳይ (የእግዚአብሔርን ህዝብ ከእጃቸው ለማዳን ሲል) በእግዚአብሔር ህልም የተሰጣቸው፣ራዕይ ያዩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አቤሜሌክ (የጌራራ ንጉስ) ስለአብርሀም፣ ስለጌድዎን የምድያም ወታደር ያየው ህልም እና በለዓም ይጠቀሳሉ፡፡
ግን ጣኦትን የሚያገለግል ሌዋዊ መልዕክቱን ከየት አመጣው ብሎ መመርመርአግባብነት አለው፡፡
የዳን ሰዎች የያዙዋት ምድርም ለኢያሱ ከተነገረው ካርታ ውጭ ናትና እግዚአብሔር ራሱን አይቃረንም፡፡
ሐ/ የአክአብ ዘመን ነቢያት
1 ነገ 22፡5-23
እነዚህ ይስቱ ዘንድ እግዚአብሔር አሳልፎ ለሰይጣን የሰጣቸው ነቢያት ናቸው፡፡ “ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክአብን የሚያሳስት ማን ነው?” በሚል ነው እግዚአብሔር ለፍርድ የተነሳው፡፡
እሺ ባይል እንጂ እግዚአብሔር በብቸኛው ነብይ በሚክያስ እውነተኛውን ትንቢትም አምጥቶለት ነበር፡- “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤እግዚአብሔርም፡- ለእነዚህ ጌታ ያላቸውም እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ” ቁ.17፡፡
መመርመር የአክአብ ፈንታ ነበር፡፡ በድምፅብልጫ ከሆነ ውሸት እና እውነት 400ለ1 ነበሩ
ኢዮሳፍጥ ተጠራጥሮ፡- “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” እንዳለው ማለት ኃጢአት ሳይሆን ብስለት ነው ቁ.7
መ/ የኤርምያስ እና የሕዝቅኤል ዘመን ነቢያት
ኤር 23፡13-32
የሰማርያ ነቢያት በበአል ስም ትንቢት ይናገራሉ (ቁ.13)፤በአል ጣኦት ነው፡፡ ከበስተጀርባው ግን አጋንንት አሉ፡፡
የኢየሩሳሌም ነቢያት ኃጢአት ይሰራሉ፤ከልባቸው አውጥተው በውሸት ይናገራሉ ቁ.14-17፤የጌታን ምክር አይሰሙም ቁ.18
ስለዚህ ገለባን ከስንዴ ለይቶ መመገብ የእኛ ፈንታ ነው ቁ.25-29
የሕዝቅኤል ዘመን ነብያትን በሁለት መመደብ ይቻላል፡-
1. ስለ ጭብጥ ገብስና ቁራሽ እንጀራ የሚተነብዩ
ሴቶች ነበሩ ሕዝ 13፡17-23
በዚህ ዘመን የሚያገኙትን ጥቅም (ገንዘብ)፣ስጦታ አይተው ሰላም በሌለበት ሰላም የሚሉትን አይነት ናቸው፡፡
2. እግዚአብሔር ለአይምሮአቸው አሳልፎ የሰጣቸው
ያሳታቸው ናቸው ሕዝ 14
ጣኦት በልቡ ለያዘ ህዝብ ሰላምን፤በረከትና እረፍትን የሚተነብዩ ናቸው
ጌታ ለሽማግሌዎቹ የላከው መልዕክት የማይለወጥ ነበር፣በኤርምያስ ለ40 ዓመታ እንደተተነበየው ያው ነበር፡- “እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል፡- ንስሐ ግቡ” ቁ.6
ከዚህ ውጪ ኖህ (ታላቁ የንስሐ ሰው)፣ኢዮብ (ንፁሁ) እና ዳንኤልን በኮንፍረንሳችሁ ብትጋብዙ እንኳን ለውጥ የለም እነሱም ያለነብሳቸው ማንንም አያድኑም የሚል ነው፡፡
ሠ/ አሳች መንፈስና የጌታ ኢየሱስ ፈተናዎች
ማቴ 4፡1-11
“እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል” ቁ.3 በራበው ጊዜ፡፡
ፀጋን ለጊዜያዊ ፍላጎታችን መገልገያ ለማዋል መፈተንን ያመለክታል፡፡
ቃል ጠቅሶ ለአጓጉል ተአምራት (ከመቅደስ ጫፍ ራስን እንዲወረውር እና እንዲተርፍ) ማነሳሳት ቁ.5-7
ቃሉን abuse ለማድረግ (አለአግባብ እንድንጠቀም) ማነሳሳትና ማሳት፣ከተፃፈበትመንፈስወጥተን እንድንተረጉመው በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ማጣላት
ከሰገደለት “የዓለምን መንግስታት ክብራቸውንም አሳይቶ”እንደሚሰጠው ተስፋ ገባለት ቁ.8-9
ጌታ መንግስተ ሰማያትን ሲሰብክ፣ሰይጣን ሁሌ መንግስተ ዓለምንና ክብሯን በመስበክ ሊያታልለን፣ ሊያስተን ይጥራል ሮሜ 4፡17፤ፊልጵ 3፡18-21፤ቆላ 3፡1-4፤የቆላስያስ ሰዎች በዚያን ዘመን ስጋን በመጨቆን ያምኑ ነበር ቆላ2፡16-23፡፡ የዚህ ዘመን የብልፅግና ወንጌል ደግሞ ተቃራኒውን ጽንፍ ይዞአል ግን ልናተኩር የሚገባን በቆላ 3፡12-17 መሰረት በላይ ኢየሱስ ባለበት ባለው ላይ ነው፡፡ያም ሰማያዊ ብልፅግና ነው፡

ረ/ አሳች መንፈስና የትክክለኛ ተአምራት ፈተናዎች ዘዳ 13፡1-5
• እግዚአብሔር ህዝቡ ቃሉን ያከብር ወይስ አያከብር እንደሆነ ለመፈተን እንደቃሉ ያልሆኑ እውነተኛ ምልክትና ተአምራት ሊልክ ይችላል፡፡ ተፈትኖ ለማለፍ ቃሉን የሙጥኝ ብለን ነቢዩን ወይም ህልም አላሚውን እንቢ ማለት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ የብሉይ ዘመን ጣኦታት ተቀርፀው የተሰሩ የአማልክት ምስሎች ናቸው፡፡ የአዲስ ኪዳኖቹየእኛ ጣኦታት ደግሞ ገንዘብ፣ሆድ/ምድራዊነትና ዓለማዊነት ናቸው፡፡ ይህንን የመጀመሪያ አድርጎ በልባችን የሚስል የትኛውም አገልጋይ ድንቅና ተአምራት ቢከተለው ልንቀበለው አይገባም፡፡
ሰ/ አሳችመንፈስና እንክርዳዶች
በማቴ7 ቁ.15 መሰረት ሐሰተኛ ነቢያት፣የበግ ለምድ የለበሱ እንጂ በግ አይደሉም፡፡አላማቸው በጎችን መብላት ነው (ጥቅም)፡፡ በቁ.16-10 መሰረት መልካም ፍሬ የላቸውም፤ከባህርያቸውም ፍሬ ሰጪ ዛፎች አይደሉም፡፡
• እንክርዳዶች ናቸው “እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፡፡ የዘራውም ጠላት ዲያቢሎስ ነው” ማቴ 13፡39፡፡
• ስለ እንክርዳዱ “ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳዱን ዘርቶ ሄደ፡፡ ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ፡፡ የባለቤቱም ባሮች ቀርበው “ጌታ ሆይ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዴንስ ከወዴት አገኘ አሉት፡፡ እርሱም፡- ጠላት ይህንን አደረገ አላቸው” ቁ.25-28፡፡ ስራው የጠላት ነው፡፡ ጠላት ደግሞ አመሳስሎ ስለሰራው ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ ነው እንክርዳዱ የታየው (ቁ.26)፡፡ የእግዚአብሔር ህዝብ ህይወቱ ፍሬ አልባ በሚሆንበት ዘመን እንክርዳዶችን መለየት ፈፅሞ አይቻልም፡፡
• ከዚህ ውጭ መከር ሳይደርስ እንክርዳድን ለመልቀም መሞከር ስንዴውን አብሮ ማጥፋትን ሊያስከትል ይችላል ቁ. 29-30፡፡
• የሆነው ሆኖ እስከመጨረሻው መከር (የዓለም መጨረሻ) ከመጠበቅ ከወዲሁ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡ ያኔ እንክርዳዱ ራሱ ያለ ፍሬ ቆሞ ይታያል፡፡
• ስለመጨረሻው ዘመን ጌታ፡- “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች፡- እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ማንም፡- እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፡- ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑሐሰተኞች ክርስቶስችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኩዋ እስኪያስቱ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” ብሎናል ማቴ 24፡4-5፤23-24፡፡
ማጠቃለያ
ይህ ዘመን ህዝብ ነቢያትን እየተከተለ ቃሉን የጣለበት ዘመን ነው፣ ነቢያቱ ቃሉን አያስተምሩትምና፡፡ የልባቸውን የመልካም ምኞት መግለጫ መፈክር ይጮኹለታል፡፡ ህዝቡም በስካር ለምድራዊ ስኬትና ብልጽግና ይሁንታውን በአሜንታ ሁካታ ይገልፃል፡፡ሐይ ባይ በሌለበት እየተከታተሉ ገደል መግባት ሆኖአል፡፡ ወደ ቃሉ ብንመለስ ይበጃል፡፡
ሐይማኖትአለን፤ግን እየሞትን ነው፡፡አይሁድ የአብርሐም ልጆች፣የእግዚአብሔር ልጆች ነን እያሉ ይመፃደቁ ነበር፡፡ ጌታ ግን “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ” ይላቸው ነበር ዮሐ 8፡44፡፡ በሙሴ ሕግና በነቢያት መጽሐፍት ላይ የተመሰረተ ጥብቅ ሐይማኖት አለን ሲሉ የዲያሎስ ልጆች ሆነው ነበር፡፡ የሐሰተኛ ነቢያትም አስተዋፅኦ አለበት፡፡አሁንም ይህ ለኛ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡መመለሱ ይበጀናል፡፡ ወደ ቃሉ፡፡
በራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ የተጠቀሰችዋ የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን ሐሰተኛ ነብይ ኤልዛቤል ህዝቡን በማሳትና ለሰይጣን ጥልቅ ሚስጥር ተብዬ በማመቻቸት የተሳካላት ነበረች፡፡ ቢሆንም ጌታ ለእርሷና ለተከታዮቿ የንሰሐን ጊዜ እንደሰጠ ለእኛም ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ እንደ ቃሉ ባልሆነ ትምህርትና አካሄድ ውስጥ ለጨመሩን ነብያትም ሆነ ለእኛ ለተከታዮቻቸው መመለስ ይበጀናል፡፡
ማሳሰቢያ
በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ነብያት የተባሉት ከቀናው መንገድ የወጡትንና ሐሰተኞችን የተመለከተ መሆኑን መግለፅ ያስፈልጋል፡፡
Disciples of Jesus/Restoration
1bible.page.tl

የተረገሙ ሰባኪያን ወንጌል


“ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ ፣ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን፡፡” (ገላ 1፡8-9)
በገላትያ ያሉ አብያተክርስቲያናት በጅማሬአቸው እንዴት እንደ ነበሩ ጳውሎስ በመልዕክቱ ሲያስታውሳቸው፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ተስሎ ነበር” ይላቸዋል (ገላ.3፡1)፡፡ ቀደም ብሎ “ በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል:: እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም፡፡ የሚያደነጋግሩአችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ” ብሎአቸዋል (ገላ. 1፡6 )፡፡
ልዩ ወንጌል ምንድነው
የተለየ ወንጌል የሚባለው የተሰቀለውን ክርስቶስ የመዳናችን (salvation) ማዕከል እንደሆነ እንዳናስተውል የሚያደርገን የተጣመመ ወንጌል ነው፡፡ ለምሳሌ የገላትያ አብያተክርስቲያናት በኢየሱስ ማመንን እንደያዙ የብሉይ ኪዳኑን የመገረዝ ሕግ እንዲጨምሩበትና ድነታቸውን እንዲያሟሉ የመከረና የአይሁድ እምነትን ከክርስትና የቀየጠ ትምህርት ነው ልዩ ወንጌል ተብሎ የተጠራው፡፡ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” ሲል ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ክርስቲያኖች በ1ቆሮ.1፡23 ላይ እንደጻፈው የእውነተኛው ወንጌል ማዕከል የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በክርስትና ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ በተሰባሰበ ጥቅስ በተደራጀ መልክ የሚሰበክ ማንኛውም ወንጌል ልዩ ወንጌል ይባላል፡፡ ሰባኪያኑም የሰማይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ የተረገሙ ናቸው፡፡
ይህ የብሉይ ኪዳን ቀያጭነት በቆሮንጦስ ቤተክርስቲያንም ሰይጣን አሽሉኮ በሾማቸው አይሁድ ክርስቲያኖች በኩል ገብቶአል (2ቆሮ.3፡13፤11፡3-15)፡፡ እንደውም ቤተክርስቲያኒቱ በሚሰበክላት “ሌላ ኢየሱስ” እና “የተለየ ወንጌል”፣ “የተለየ መንፈስ” እየተቀበለች ነገሩን በቸልታ አልፋዋለች ( 2ቆሮ.11፡4)፡፡
የዘመናችን የተረገሙ ሰባኪያን ወንጌል የቱ ነው
ይህ ከላይ ያነሳነው ብሉይ ኪዳናዊ ቀያጭነት በድንቅና ተአምራት ታጅቦ በሰይጣን አቀናባሪነት (2ቆሮ.11፡13-15) በብዙ ውዳሴ በፕሮቴስታንት መድረክ ላይ ገኖአል፡፡ ቤተክርስቲያን ከሙሴ ሕግ በታች አይደለችም ብሎ ያለን አዲስ ኪዳን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጌታ ከተደገሙት የፍቅር(ማቴ.22፡35-40) ፣ የአስርቱ ትዕዛዛት (ማቴ.5፡17-44) እና የአስራት ሕግ (ሉቃ.11፡42) በቀር የዘዳግም 28 የበረከትና መርገም ሕግም ለእስራኤል የተሰጠ እንጂ ለቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ መገረዝ ለጤና ከሆነ እንጂ ለጽድቅ ቀርቶአል እያልን ዘዳግም 28 ግን አልቀረም ብንል ተሳስተናል፡፡ በእርሻችን ሁለት አይነት ዘር እንዳንዘራ፣ ከሁለት አይነት ነገር የተሠራ ልብስ እንዳንለብስ ተነገረውን ሕግ ለእሥራኤል እንጂ ለቤተክርስትያን እንዳልሆነ አንከራከራለን፡፡ የዘዳግም28 በረከቶችን ግን የብልጽግናችን መሠረት አድርገን እንሰበካለን፣እንሰብካለን፡፡ ትልቅ ስህተት!
የዘመኑ የበረከት፣ የስኬት፣ የጤና እና የብልጽግና ሰባኪያን መሠረት ዘዳግም 28 ነው፡፡ የተሰቀለውን ክርስቶስ ከሙሴ ሕግ ቀይጠው ልዩ ወንጌል እንዲሰብኩ ሰያጣን የሾማቸው (2ቆሮ.11፡13-15) እግዚአብሔር ግን የረገማቸው ናቸው፡፡ “ እስራኤላውያን የፊቱ ማንጸባረቅ እየጠፋ ሲሄድ መጨረሻውን እንዳይመለከቱ ፊቱን በጨርቅ እንደ ሸፈነው እንደ ሙሴ አይደለንም፤ ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተነበበ ቁጥር ያ መሸፈኛ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልተወገደ ልቡናቸው እንደደነዘዘ ነው፤ መሸፈኛው አሁንም አልተወገደም፤የሚወገደው በክርስቶስ ነውና፡፡ እስከ ዛሬም የሙሴ ሕግ በተነበበ ቁጥር መሸፈኛው ልቡናቸውን ይሸፍናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል፡፡” (2ቆሮ 3፡13-16)
የቤተክርስቲያን ልቡና ዛሬም በነዚህ የተረገሙ ሰባኪያን ያ የብሉይ ኪዳን መሸፈኛ ተጥሎበት ደንዝዞአል፤ ክርስቶስንም መስቀሉንም መመልከት ተስኖታል፡፡ ስኬት፣ ብልጽግና እና ጤና ጣኦት ሆኖበታል፡፡ ቤተክርስቲያን የምድራዊ ነገር ምኞች አስክሮአታል፡፡ “ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና፡፡ አመንዝሮች ሆይ፣ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” (ያዕ.4፡3-4)፡፡ በተጨማሪ 1ዮሐ.1፡15-17 ይህንኑ ይደግምልናል፡፡
እነዚህ ሰባኪያን “መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ልባቸው ያረፈው በምድራዊ ነገር ላይ ነው” ፊሊጵ.3፡19፡፡ ቁጥር18 “ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ” እንደሚል እንዲሁ የመስቀሉ ጠላቶች ሲሆኑ ነገር ግን የምድራዊ ነገር ወዳጆች ናቸው፡፡ የሕዝቡ ልብ ከመስቀሉ ይልቅ በምድራዊ ነገር እንዲያዝ ለማድረግ በትጋት እንዲሰሩ ሰይጣን በድንቅና ተአምራት ያጅባቸዋል፤ ከሕዝብ የሚዘርፉት ሰአራትና ስጦታ አበልጽጎአቸዋል (2ቆሮ.11፡20)፡፡ ሕዝቡ እንደነሱ”ሊባረክ” እያጨበጨበ በረከተ-መርገማቸውን “አሜን!” እያለ ይከተላቸዋል፡፡ ግን የተረገሙ ናቸውና ከመንገዳቸው ተመልሶ ንሰሐ ይገባ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የምድራዊ (ዓለማዊ) ነገር ወዳጅ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ይላል፤ ጌታንና መስቀሉን አይወድም፡፡ “ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን” ይላል የእግዚአብሔር ቃል 1ቆሮ. 16፡22፡፡ የተባረክን መስሎን ከገባንበት እርግማን በንስሐ እንመለስ፡፡ “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል፡፡ እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም፡፡” (ማቴ 6፡24)
እስራኤል ለምርኮ የተዳረገችበት ኃጢአቶች፡- (1)ጣኦት አምልኮ፣ (2) የማህበራዊ ፍትህ መጉደልና (3) እነዚህ ኃጢአቶቹዋን ለመሸፈን የምታደርገው የአምልኮ (የመስዋዕት) ማደናገሪያ ነበሩ፡፡ በተለይ ሦስተኛውን ማለትም ይህንን አምልኮ እንደሚጸየፍ ጌታ ደጋግሞ ይነግራቸው ነበር፤ ኢሳ.1፡11-17 እና ሚል.1፡10 ቢነበብ፣ ጌታ ምን ያህል በዚህ አምልኮ እንደተንገሸገሸ እንረዳለን፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ በምድራዊ ጣኦቶችና በኀጢአት ተይዘን በዝማሬ ሁካታና ግርግር እግዚአብሔርን ለማደናገር በመሞከር ላይ ተጠምደናል፡፡ እስራኤልና ይሁዳን ይህ በጠላት ምርኮ ከመወሰድ አላዳናቸውም፡፡ እኛም ከመሸነፍ፣ ከመዝቀጥና በሰይጣን ከመማረክ አናመልጥም እየዘመርን ፣ እየጨፈርን! ስለዚህ ንስሐ!

የትንቢት ገለባ

«ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? በውኑ ቃሌ እንደ እሳት ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር፡፡ስለዚህ እነሆ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነብያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እነሆ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እነሆ ሀሰትን በሚያልሙ በሚናገሩም በሀሰታቸውና በድፍረታቸው ሕዝቤን በሚያስቱ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እኔም አልላክኋቸውም ፣ አላዘዝኳቸውም ለእነዚህም ህዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም ይላል እግዚአብሔር» ኤር 23፡28-32፡፡ ህዝቡን /እስራኤልን/ እህል ሳይሆን ገለባ የሚያበሉ ፣ እግዚአብሔር የሚቀጣቸው ሶስት ዓይነት ነቢያት ተጠቅሰዋል፡- /1/ እርስ በእርስ ቃል በመሰራረቅ የሚሰብኩ /የሚተነብዩ/፣ /2/ አፈጮሌዎች /አ.መ.ት/ እና /3/ ሀሰተኛ ህልም ተመርኩዘው ትንቢት የሚናገሩ /አ.መ.ት/ ናቸው፡፡ እነዚህ ህዝቡን ከእግዚአብሔር መንገድ በማውጣት ትልቅ በደል መፈጸም ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ለውድቀትና በባቢሎን ኃይል ተማርኮ ከአገሩ ለመፈናቀል ዳርገውታል፡፡
በዘመናችንም እንዲሁ ተሰራርቆ መስበክ፣ ከመጽሀፍ የሰረቁትን መስበክና ማስተማር የተለመደ ነው፡፡ አፈጮሌ የኮንፈረንስ ስታሮች በነቢያትነት አገሪቷን ከዳር እስከ ዳር ናኝተውባታል፡፡ የህዝቡን ጀርባ እንዴት እንደሚያኩለትና እንደሚያስፈነድቁት አንደበታቸው ጥበቡን ተክኖታል፡፡ የህዝቡን ስሜት ኮርኩረው በደስታ ያሰክሩታል፡፡ ክፋቱ ስካሩ ከሰኞ ጠዋት ያለማለፉ እንጂ፡፡
መድረኩ እነዚህን ይፈልጋል፣ ካለበት እያሰሰ ለኮንፈረንስ ወረፋ ያስይዛቸዋል ፣Entertainment ነዋ! እሁድ ከሰአት የስጦታ ጊዜ ይባልና በጮሌ ምላስ ህዝቡን አስቤዛውን ያስተፉታል፡፡ መሪዎች ደስ ይሰኛሉ፡፡ በአመፀኝነት ለምናውቃቸው መሪዎች እንዴት ያለ አስደናቂ ቡራኬ፣ አድናቆትና፣ የትንቢት ድምጽ በማምጣት እኛንም በምቀኝነታችን ያሸማቅቁናል፡፡ እንዲህ ይቀለድና ዳጎስ ያለ ገንዘብ በፖስታ ተይዞ ይኬዳል፡፡ ለወደፊቱም ፕሮግራም አስይዞ፡፡
እውነተኛ ትንቢቶችና ራዕዮች የመኖራቸውን ያህል እንዲሁ ሀሰተኞች ደግሞ ከመድረክ እስከ ጓዳ የጴንጤውን ዓለም አጨናንቀውታል፡፡ እንደመደብር በየቦታው ቤተእምነት ለመፈልፈል፣ የማይፈልጉትን ሰው ስም ለማጥፋትና ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ፣የኮትሮባንድ ነጋዴዎችን ሳይቀር ለአመፀኞች ቡራኬ በመስጠት ከእነርሱ በሚገኘው ኑሮን ለመደጎም፣ አረ ስንቱ! ህዝቡም በዚህ ሱስ ተለክፎአል፡፡ ትላንት ተሸውዶ ዛሬም ይታለላል፡፡ እንደ ህመም ማስታገሻ ትንሽ ቅር ሲለው ሱሱን ለማስታገስ ይሮጣል፣ ይራወጣል፡፡ እረፍት አጥቶአል፡፡ እያሳደደ ገለባ ይበላል፡፡ ቃሉን / መፅሐፍ ቅዱስን / ስታስተምረው ወይም ስትሰብከው የፕሮግራም ማሟያ ስለሚመስለው አይሰማም፡፡ ያዛጋዋል፣ ያቁነጠንጠዋል፣ የለመደውን የሱስ ማስታገሻ ፍለጋ፡፡ እንግዲህ በአጭሩ ጴንጤነት ከቃሉ ይልቅ በትንቢት ላይ መመስረት ሆኖአል፡፡ ስለዚህ ወደ ቃሉ ካልተመለሰ ከስሮአል፡፡