Sunday, July 26, 2015

ሐዋርያቱ ደቀመዛሙርት እንጂ ሐይማኖተኞች አልነበሩም


የጌታ ኢየሱስ ሐዋርያት ጴንጤም፣ ኦርቶዶክስም፣ካቶሊክም አልነበሩም፡፡ እነርሱ ጌታን በፍጹም አምላክነቱ እና ሰውነቱ ተረድተውት መዳን በእርሱ ብቻ እነደሆነ ሰብከውና አስተምረው ያለፉ ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡ በውስብስብ የስነመለኮት ጥያቄዎች ውስጥ እራሳቸውን ዘፍቀው ሲፈላሰፉ እና ሲከራከሩ የኖሩ አይደሉም፡፡ በወቅቱ ለተነሱ የስነመለኮት ጥያቄዎች እና የኑፋቄ ትምህርቶች እንደቃሉ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ያለፈ ነገር ውስጥ አልገቡም፡፡
ከእነርሱ በኋላ ጥቂት መቶ አመታት ቆይቶ በተነሱ አባቶቸ ዘመን ነው የስነመለኮት ውስብስብ ፍልስፍናዎችና ክርክር ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል የዳረጓት፡፡ በ5ኛው ክ/ዘ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወደ ኦርቶዶክስነትና ካቶሊክነት ያመራው ጭቅጭቅ ከረረ፡፡ በ16ኛው ክ/ዘ ደግሞ ፕሮቴስታንት ከካቶሊክ ወጣ፡፡ ከዚያ በኋላ እስከአሁን ባለው ዘመን ደግሞ የፕሮቴስታንት መበጣጠቅ ቀጠለ፡፡እንዳውም ሲበጣጠቁ አሁን አሁን «እግዚአብሔር ተናገረኝ፣ራዕይ ሰጠኝ»በሚል ሽፋን ነው፡፡
ይህ አይነቱ እግዚአብሔር ፣ ቃሉን የሚፃረር እግዚአብሔር፣ እርሱ ልበወለድ አምላክ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ግን፣ እርሱ ቃሉን የሚያከብር፣ ሐዋርያቱን በአንድነት ያኖረ ፣ የአንድነት አምላክ ነው፡፡
ሐዋርያቱ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ በ451 ዓ.ም /በእኛ አቆጣጠር/ በኪልቄዶን ጉባኤ በተከሰሰው ያለመግባባት የእስክንድሪያ /የግብጽ/ የእምነት አባቶች ከሮም የእምነት አባቶች ሲለያዩ እና ኦርቶዶክስና ካቶሊክ የሚሉ ቃላት የተከፋፈሉ ቤተእምነቶችን በመወከል በመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ በ1054 /እ.ኤ.አ/ የምስራቅ ኦርቶዶክስ ከሮም ካቶሊክ ሊለያዩ፣ ኦክቶበር 31፣1517 ሉተር 95 የልዩነት ነጥቦችን በዊትንበርግ ባለችው ቤተክርስቲያን በር ላይ ለጥፎ ከካቶሊክ ሲወጣ እና ለጴንጤነት መሰረት ሲጥል፣ከዚያ በኋላ ደግሞ ብዙ ቤተእምነቶችና /የእምነት ክፍሎች / Sects / በጥቃቅን ልዩነቶች ጴንጤነትን ሲበጣጥቁት፣ የየቱ አባል ይሆኑ ነበር ብላችሁ ታስባላችሁ?
ለእነርሱ ሁሌም ትክክለኛ መንገድ ኢየሱስ ፣መጽሐፍ ቅዱስና የደቀመዛሙርት አንድነተ ነው፡፡ ትክክል ያልሆነውን ትምህርት በትክክለኛው ያፈርሳሉ፣ ኑፋቄንያወግዛሉ፡፡ ግን ትክክል የሆነውም ደቀመዝሙር ሆኖ ደቀመዛሙርትን ለክርስቶስ እንዲያፈራ መንገድ ያሳዩታል እንጂ አንተ በያዝከው አንጃ ተከታዮችን እያፈራህ ቀጥል አይሉትም፡፡ ምክንያቱም «እኔ የጳውሎስ፣ እኔ የኬፉ፣ እኔ የአጰሎስ፣ እኔ ደግሞ የክርስቶስ » የሚል የአንጀኝነት አካሄድ አልተፈቀደምና ነው፡፡
እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው ከስነመለኮትና ስነአመራር ውስብስብ ቀመር ይልቅ ደቀመዝሙር ብቻ ሆነን የክርስቶስን የህይወት ምሳሌ እንድንተገብር እያሳዩን ያሳርፉን ነበር፡፡
ለምሳሌ ሙሉ ወንጌል ከሙሉ ወንጌል/፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አብያተ እምነት /ዲኖሚኔሽኖች/ አመራር፣ ላይ ላዩን እንጂ ፍጹም አንድነት ፍጹም የማይታሰብ ነው፡፡ አዳዲስ ከሚፈለፈሉትማ ጋር ጠቡ እና ሽኩቻው የከረረ ነው፡፡
አንድ ጴንጤ እሁድ አጠገቡ ያለውን የእርሱ ያልሆነ ቤተእምነተ አልፎ የእኔ ወደሚለው ለመሄድ በታክሲም በእግርም ስንት ርቀት አቆራርጦ በመሄድ ያመልካል፡፡ የአጥቢያ አመለካከት በኦርቶዶክስ እንኩዋ እንዲህ አይደለም፣ ሁሉም በሚቀርበው ደብር ነውና የሚሰበሰበው ልዩ ፕሮግራም ካልሆነ በቀር፡፡ አንዱ ለፍቶ ያስተማረውን ሌላው የጴንጤ «ቤተክርስቲያን»ከወሰደ ቅሬታ ይፈጠራል፣ከተደጋገመ ከማስኮብለል ይቆጠራል፣ ከጨመረ ግን በነፍሳት ዘረፋ ይከሰሳል፣«ዘራፊው» የአብያተ ክርስቲያናት ህብረት አባል ከሆነ፡፡
እና ሐዋርያቱ የዚህ አይነት እቃእቃ ጨዋታ አካል ይሆኑ ይመስላችኋል?
እነርሱ ጴንጤም፣ካቶሊክም፣ ኦርቶዶክስም አልነበሩም፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ አንድነትዋን ጠብቃ በኖረች ኤክሌሺያ እንጂ አባልነታቸው በድርጅት ውስጥ አልነበረም፡፡

Disciples of Jesus/Restoration

1bible.page.tl 

No comments:

Post a Comment