Sunday, July 26, 2015

ብሉይ ኪዳናዊ ጴንጤነትና ወጥመዱ



የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን (የኢትዮጵያዋን ማለቴ ነው) በብሉይ ኪዳን የታቦት ሥርዓትዋ ስትተች የኖረች የፕሮቴስታንት እምነት በተራዋ በብሉይ ኪዳን አስተምህሮዎች ተተብትባለች፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ለህዝብ በሚስማማ መልክ ተቀምሮ ይቀርባል፡፡
አዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ሲበረዝ ለብዙዎች ስሜት ተስማሚ ሆኖ ስለተገኘ ለመቃወም ጉልበት ጠፋ፤ አሮጌው ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ከሰመረ ምድራዊውን ብልጽግና እና ስኬት እንደሚያንበሸብሽ የታወቀ ነው፡፡ ጤና ፣ ቤተሰብ፣ እርሻ፣ በረት ይባረካል፣ ጠላት ይገዛል ወዘተ….፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ካልሰመረ ደግሞ መርገም አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህ የአሮጌው የእስራኤል ኪዳን አሰራር ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ብዙው በምድራዊ ትሩፋት ላይ ያተኮረ ሆኖ እስራኤልን እስካሁን አዲሱን ኪዳን እንኩዋ ሳትቀበል በብልጽናና በመፈራት እያኖራት ይገኛል፡፡ በአባቶች መታዘዝ የዛሬው ትውልድ ይኸው በሞገስ ይኖራል፡፡
ጌታ ኢየሱስም ዓላማው ይህን ለምድር ማዳረስ ቢሆን ኖሮ መምጣትና በመስቀል መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ምድራዊ ብልጽግናና ስኬትን በነዚያው የእስራኤል ነቢያት በኩል ለምድር በኤክስቴንሽን መልክ ማስፋፋት ይችል ነበር፡፡ ብሉይ ኪዳን ከምድራዊ ብልጽግናና ስኬት አንጻር ምንም አልጎደለው፡፡ ስለዚህ እርሱኑ ወደ ምድር ሁሉ ማስፋፋት ይበቃ ነበር፡፡ ጠንክሮ መስራትም ሌላው መፍትሄ ነው፡፡
ቻይና ይህ ፅሑፍ እስከ ተጻፈበት ድረስ በመንግስት ደረጃ ወንጌልን እያሳደደችና እየገፋች ነው፣ ግን የዓለምን ኢኮኖሚ በሁለተኝነት እየመራች ትገኛለች፡፡ በሶስተኛነት የምትከተለዋ ጃፓንም ያለወንጌል በልጽጋለች፡፡ ጣኦት እያመለኩ እንኳ ጠንክረው ሰርተው በልጽገዋል፡፡ ህንድንም እንዲሁ ለቁጥር የሚያታክቱ ጣኦቶች ባለቤት ሆና ሳለች እየበለጸገች ነው፡፡
ነገር ግን የሰው ልጅ የጎደለው መንፈሳዊ ብልጽግና ነበር፡፡ ሌባ በማይሰርቀው፣ ብል በማይበላው በሰማይ የሆነ መዝገብ (ሀብት) ይጎድለው ነበር፡፡ ለዚህ ነው ጌታ መንግስተ ሰማያትን የሰበከው፡፡ አዲስ ኪዳን ወደ ሰማይ ያተኩራል፣ ወደ መንፈሳዊው የእግዚአብሔር ዓለም ብልጽግና፡፡
በሁለቱ ኪዳኖች መካከል መምታታትና መሳከር በፕሮቴስታንት አብያተ እምነት ውስጥ በእጅጉ ጎልቶ እየታየ መጥቶአል፡፡ አዲስ ኪዳናዊ ጸጋ ስጦታዎችን የብሉይ ኪዳን ተስፋዎችን ለማስተማር በተሳሳተ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ሰው ጌታ ኢየሱስን ሲከተልና በህይወቱ እየመሰለው ለመሄድ ሲጨክን መከራና ስደት እንደሚገጥመው አዲስ ኪዳን ቀልጭ አድርጎ አስቀምጦታል ማቴ 5፡11-12፤ ሉቃ 14፡27 ፤ ዮሐ 16፡33፤ 2ጢሞ 10፡12፡፡
ይህንን በዘመናዊው የፕሮቴስታንት ሐይማኖት ውስጥ መስበክ ግን ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ሆኖአል፡፡ ዘዳግም 28 ላይ የተገለጹትን የመታዘዝ በረከት ዝርዝሮች በመድረክ ላይ በመጮህ የአዲስ ኪዳኑ እውነት እንዲጣፋና አደብ እንዲገዛ ይደረጋል፡፡ የጌታን ደም በምድራዊ ብልጽግናና ስኬት መመንዘር እንዴት ያለ ትልቅ መሳት ነው! የአፍሪካዎቹን ጥቂት መልቲ ሚሊየነር የጸጋ ነጋዴ ፓስተሮች ተከትሎ አብሮ ገደል ለመግባት መራወጥ አይገባም፡፡ እውር እውርን ቢመራው ሁለቱም ተያይዘው በገደል እንደሚወድቁ ጌታ ስለ ፈሪሳውያን እና ተከታዮቻቸው ከተናገረው መማር ይገባናል ማቴ 15፡14 ፡፡ ድንቅና ተአምራት አደናግሮን ከሆነ ሰይጣን እንኩዋን ድነው ወደ ገንዘብ ባርነት ለገቡ አገልጋዮች ይቅርና፣ ባልዳኑ ሐሰተኛ ነብያት ተጠቅሞ በጌታ ሥም ብዙ ሊሠራ እንደሚችል ከማቴ. 7 ፡ 15-23 መረዳት አይከብድም፡፡
የሚያሳዝነው ህዝቡም በድንጋያማው መሬት ላይ እንደ ተዘራው ዘር ከመከራና ስደት ነጻ የሚያደርገውን ስብከትና ትምህርት ሲያሳድድ፣ በእሾህ መካከል እንደ ተዘራ ዘር ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያለ ፍሬ እየቀረ ነው (ማቴ 3፡20-22)፡፡ ጌታ ኢየሱስንና መስቀሉን የሚመለከትበት የውስጥ አይኑ በዚህ ተጋርዶአል፡፡
“እንግዲህ ይህን የመሰለ ተስፋ ፣ ስላለን ፣ በድፍረት እንናገራለን፡፡ እስራኤላዊያን የፊቱ መንፀባረቅ እየጠፋ ሲሄድ መጨረሻውን እንዳይመለከቱ ፣ ፊቱን በጨርቅ እንደሸፈነው እንደ ሙሴ አይደለንም፡፡ ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተነበበ ቁጥር ያ መሸፈኛ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልተወገደ ልቡናቸው እንደደነዘዘ ነው፣ መሸፈኛው አሁንም አልተወገደም፣ የሚወገደው በክርስቶስ ብቻ ነውና፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ የሙሴ መጽሐፍት በተነበቡ ቁጥር መሸፈኛው ልቡናቸውን ይሸፍናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል” 2ቆሮ 3፡12-16፡፡ ስለ መዳን ቢሆንም፣ መጽሐፍ የሚለን የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች ላይ ብቻ መንተራስ ያሳውራል፣ መንፈሳዊ ድንዛዜ ያስከትላል ነው፡፡
ከብሉይ ኪዳን እንማራለን፣ እንሰበካለን፡፡ ምክንያቱም የእግዜአብሔር ቃል ነውና ዛሬም ወደፊትም ጥንትም እንደሰራው ይሰራል፡፡ ግን ከአዲስ ኪዳን ተስፋዎችና መርሆዎች ጋር ሳይቃረን መሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ብሉይ ኪዳን የተቀቡ የእግዚአብሔር ሰዎችንም ያልቅ ነበር ዘፍ 12፡2 ፤ መዝ 89፡19-37፡፡ አዲስ ኪዳን ግን ክብርን ለኢየሱስ ብቻ ይሰጣል፡፡ የዘመኑ አገልጋዮች የክብር እና የዝና ሽሚያ ይህን ያገናዘበ አይደለም ዮሐ 3፡30፡፡
ሲጠቃለል ዘዳግም 28 ለእስራኤል የተሰጠ የተስፋ ቃል ነው፡፡ በአሮጌው ኪዳን መሠረት ውል ተጋቢዎቹ እግዚአብሔርና እስራኤል ቃል ኪዳን ሲቋጥሩ የተፈራረሙበት ሰነድ ነው፡፡ አዲስ ኪዳን ግን በቤተክርስቲያንና በእግዚአብሔር መካከል በጌታ ደም አማካኝነት የተቋጠረ ውል ነው፡፡ ስለዚህ የሁለቱን ኪዳኖች የተስፋ ቃሎች ማደባለቅ አይቻልም፡፡
ጌታ፡- “ ንሰሐ ግቡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ” እያለ የሰማይ መንግስትን ሰበከ (ማቴ 4፡17)፡፡ የሰይጣን ቋንቋ ደግሞ አንድ ነው፡- “ የዓለምን መንግስት ከነክብራቸው አሳየውና ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ አሰጥሃለሁ” አለው የሚል ነው ማቴ. 4 ፡ 8-9 ( የአጽንኦት መስመር የእኔ ነው) ፡፡ ምርጫችን ወይ የዓለም መንግስት ወይም የሰማይ መንግስት ይሁን ፡፡ ሁለት ወዶ አይሆንምና ብሉይ ኪዳንን አስታኮ ከመጣብን ስውር የሰይጣን ወጥመድ ማምለጡ ይበጀናል፡፡
Disciples of Jesus/Restoration

1bible.page.tl  

No comments:

Post a Comment