Sunday, July 26, 2015

አሳሳች ድንቅና ተአምራት


ሰው በባህሪው ከአማልክት ልዕለ ተፈጥሮአዊ ምልክቶች ማየትይፈልጋል፡፡ እስራኤላውያን ጌታን ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ይጠይቁት እንደነበር መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡«መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ» ይላል 1ቆሮ 1፡22፡፡
እውነተኛ ድንቅና ተአምራት የመኖራቸውን ያህል ተመሳስለው የሚሰሩ መኖራቸውን ካላወቅን ተሳስተን ማለቃችን ነው፡፡ እነዚህም፡-
1. ከእግዚአብሄር ለፈተና እና ለፍርድ የሚላኩ ዘዳ 13፡1-4እነዚህ ነቢያት በብሉይ ኪዳን ዘመን ድንቅና ተአምራትን እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ግን ከቃሉ ባፈነገጠ መንገድ የሚሰሩ መሆናቸውን መርምሮ መቀበልና መጣል ለህዝቡ የተተወ ነው፡፡ ምክንያቱም ነብያቱ ሌሎችን አማልክት ለማምለክ ህዝቡን ያነሳሱ ነበርና እነሱን መከተል ያለመከተሉ እግዚአብሄርን የመውደድም ሆነ ያለመውደዱ መፈተኛ ነበርና ነው፡፡
በአዲስ ኪዳን የምንሰግድለት ተቀርፆ የተሰራ ጣኦት የለም፡፡ ግን ገንዘብና ሆድ ጌታ ሊሆኑ እንደሚችሉ በግልጥ ተነገሮናል፡፡ ከኢየሱስ በላይ የቤተክርስቲያናችንን ወይም የልባችንን መድረክ የገዛ ነገር እርሱ ጣኦታችን ነው፡፡ ለምሳሌ የብልፅግና ወንጌል ሰባኪያን መድረክ ከኢየሱስ በላይ በገንዘብና ጤና ስኬት ስብከት ተይዞአል፡፡ ስለዚህ ምድራዊ ስኬት በብልጽግና ወንጌል ወይም የእምነት ቃል ሰባኪያን ዘንድ ጣኦት ነው፡፡ እንግዲህ እዚያ ስፍራ ባሉ ነቢያትና ፓስተሮች ምንም ያህል ድንቅና ተአምራት ቢሰራ ልንታለል አይገባም፡፡ ልንቀበላቸውም አይገባንም፡፡ ገንዘብ ጣኦታቸው ነውና፡፡
ምክንያቱም የድንቅና ተአምራቱ ምንጭ ሰይጣን ነው፡፡ በተለይ በመጨረሻው ዘመን እውነት የሆነውን የእግዚአብሄር ቃል የሚገፋ ትውልድ ለዚህ ፍርድ ተጋልጦ እንዲሰጥ እና እንዲታለል የሚፈቅድ ራሱ እግዚአብሄር ነው፡፡ «በዚህም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፣ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ የገለጣል፣ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉ እና በምልክቶች በሀሰተኞች ድንቆችም በአመፅም መታለል ሁሉ እንደሰይጣን አሰራር ነው፡፡
ስለዚህም ምክንያት፣ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በአመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፣ ሀሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሄር የስህተትን አሰራር ይልክባቸዋል» 2 ተስ 2፡8-12፡፡
ስለ አክአብና ስለ ነቢያቱ፡- «መንፈስም ወጣ በእግዚአብሄርም ፊት ቆሞ፡- እኔ አሳስተዋለሁ አለ፡፡ እግዚአብሄርም ፡- በምን? አለው፤ እርሱም፡- ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሀሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ፡፡ እግዚአብሄርም፡-ማሳሳትስ ታሳስተወለህ ይሆንልሃልም ውጣ፣ እንዲሁም አድርግ አለ፡፡ አሁንም እነሆ፣ እግዚአብሄር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሀሰተኛ መንፈስ አድርጎአል…» የተባለው ምንድነው? በንጉሱ በአክአብ ላይ ለፍርድ የወጣ አሳሳች መንፈስ /ሰይጣን/ ነቢያቱን መቆጣጠሩን ከዚህ ከ1ነገ 22፡21-23 እንረዳለን፡፡ ሰይጣን በበሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሄር ፊት ቀርቦ ይነጋገር እንደነበር ከመጽሀፈ ኢዮብ እንረዳለን፡፡ ስለ ሳኦልም፡- «የእግዚአብሄርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፣ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሄር ዘንድ አሰቃየው» የሚለው እንዲሁ ሳኦል በአመፅ ለሰይጣን ተላልፎ መሰጠቱን የሚያሳይ ፍርድ ነው 1ሳሙ 16፡14፡፡
ዛሬ ለዚህ ስህተት አሰራር የተጋለጡ አብያተ እምነቶች በኢትዮዽያ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት እና ቪዥነሪ አብያተክርስቲያናት ህብረት ውስጥ በአባልነት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ በሳተላይት ዲሽም የምንከታተላቸውን ፕሮግራሞች ከዚህ አንፃር እያጣራን መቀበል ይገባናል፡፡ የዘወትር ስብከታቸው ኢየሱስ ሳይሆን የሀብትና የጤና ስኬት የሆነ ነቢያትና ፓስተሮች ድንቅና ተአምራት ሲሰሩ ብናይ መንፈሳችንን መጠበቅ ይገባናል፡፡
1. 2. የበግ ለምድ በለበሱ ነቢያት የሚሰሩ ድንቅና ተአምራት
ማቴ 7፡15-23 እነዚህ ነቢያት ተኩላዎች ናቸው፣ የበግ ለምድ ለብሰው ከበጎች ተቀላቅለዋል፡፡ አላማቸው በጎችን መብላት ነው፡፡ ክፉ ፍሬ በሚያበቅሉ ክፉ ዛፎች ተመስለዋል፡፡ መልካም ፍሬ የላቸውም፡
ግን ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ ይላሉ፣ የእግዚአብሄርን ፍቃድ ግን አያደርጉም፡፡ ኢየሱስን ይሰብካሉ ግን ዓመፀኞች ናቸው፡፡ ገንዘብ ሀብትና ዝና ነው አላማቸው፡፡ በጌታ ስም ትንቢት ይናገራሉ፣ አጋንንትን ያወጣሉ፣ ድንቅና ተአምራትም ያደርጋሉ፡፡ ግን በጌታ የታወቁ/የዳኑ/አይደሉም፡፡ጌታም ድንቅና ተአምራት ስለማድረጋቸው አልተከራከራቸውም፡፡ የነገራቸው በእርሱ ያልታወቁ እና አመጸኞች መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡
ከዚህ የምንረዳው ሰይጣን አስመስሎ በመቀባት ነቢያትና ፓስተሮችን ሊያስነሳ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ድንቅና ተአምራቱ የእርሱ መሆናቸው እንዳይነቃ የጌታን ስም እንዲጠሩ ያደርጋል፡፡ እነዚህ በስንዴው ማሳ መካከል ዲያብሎስ የዘራቸው እንክርዳዶች ናቸው፡፡ ፍሬ እስኪያወጣ ድረስ ስንዴው ከእንክርዳዱ እንደማይለይ ሁሉ እነዚህን ነቢያት ከእውነቶቹ መለየት ያዳግታል፡፡
ለመንቀል እንኩዋ ሙከራ ቢደረግ ስንዴውን በስህተት አብሮ የመንቀል ስህተት ሊሰራ ስለሚችል እስከመከር ጊዜ /መጨረሻው ዘመን/ አብረው እንዲቀጥሉ ተፈቅዶአል /ማቴ 13፡ 24-30፣ 36-43/፡፡ ድንቅና ተአምራት በበዛባት የቆሮንጦስ ቤተክርስቲያን መካከል ሰይጣን እንደዚህ አይነት ሀዋርያትን አስርጎ አስገብቶ ነበር፡፡ «እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሀዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፣ ውሸተኞች ሀዋርያትና ተንኮለኛ ሰራተኞች ናቸውና፡፡ ይህም ድንቅ አይደለም፡ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልዓክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም …» 2ቆሮ 11፡13-15፡፡ እነዚህ ሐዋርያ ተብዬዎች ጳውሎስን ተቀባይነት እስኪያሰጡት ድረስ ዋነኛ ሐዋርያት ተብለው በቤተክርስቲያኒቱ ስፍራ አግኝተው ነበር፡፡
ጌታ የድንቅና ተአምራት አምላክ ነው፣ እውነተኛ ድንቅና ተአምራት ዛሬም አሉ፡፡ እውነተኛ ነቢያትም አሉ፡፡ ነገር ግን በዚያው መጠን ለፍርድና ለፈተና የተላኩ እና ሰይጣን አመሳስሎ እነርሱ እንኩዋን ሳያውቁት የሚጠቀምባቸው አገልጋዮች የብልፅግና ወንጌልን ስህተት ሰተት አድርገው በመካከላችን አስገብተው ድንቅና ተአምራት የሚሰሩ አሉ፡፡ ስራቸው ክፉ መሆኑን እያወቅናቸው /ዝሙት እየሰሩ፣ ገንዘብ ከቤተክርስቲያን እያጭበረበሩ ፣ መለያየትን እየዘሩ እና ቤተክርስቲያን እየከፈሉ/ ድንቅና ተአምራት የሚከተላቸው አሉ፡፡
«ጌታ ለህዝቡ ሲል እየተጠቀመባቸው ነው» የሚለውን የየዋህነት አካሄድ ትተን ብንመረምራቸው መልካም ነው፡፡ የድንቅና ተአምራቱ ምንጭ ሰይጣን ነው፡፡ የምንመረምራቸው ደግሞ ፡-
ሀ. በቃሉ
ለ. መናፍስትን በመለየት የፀጋ ስጦታ
ሐ. መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ስለሚመረምር መንፈሳዊ
ክርስቲያን በመሆን
መ. በፍሬአቸው
ሠ. የመገለጡ /ድንቅና ተአምራቱ/ ክብር ለኢየሱስ መሆኑን በማረጋገጥ ሊሆን ይችላል፡፡
ክብር ሁሉ ለነገስታት ንጉስ ለጌታ ኢየሱስ ይሁን!


No comments:

Post a Comment