Sunday, July 26, 2015

የትንቢት ገለባ

«ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? በውኑ ቃሌ እንደ እሳት ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር፡፡ስለዚህ እነሆ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነብያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እነሆ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እነሆ ሀሰትን በሚያልሙ በሚናገሩም በሀሰታቸውና በድፍረታቸው ሕዝቤን በሚያስቱ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እኔም አልላክኋቸውም ፣ አላዘዝኳቸውም ለእነዚህም ህዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም ይላል እግዚአብሔር» ኤር 23፡28-32፡፡ ህዝቡን /እስራኤልን/ እህል ሳይሆን ገለባ የሚያበሉ ፣ እግዚአብሔር የሚቀጣቸው ሶስት ዓይነት ነቢያት ተጠቅሰዋል፡- /1/ እርስ በእርስ ቃል በመሰራረቅ የሚሰብኩ /የሚተነብዩ/፣ /2/ አፈጮሌዎች /አ.መ.ት/ እና /3/ ሀሰተኛ ህልም ተመርኩዘው ትንቢት የሚናገሩ /አ.መ.ት/ ናቸው፡፡ እነዚህ ህዝቡን ከእግዚአብሔር መንገድ በማውጣት ትልቅ በደል መፈጸም ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ለውድቀትና በባቢሎን ኃይል ተማርኮ ከአገሩ ለመፈናቀል ዳርገውታል፡፡
በዘመናችንም እንዲሁ ተሰራርቆ መስበክ፣ ከመጽሀፍ የሰረቁትን መስበክና ማስተማር የተለመደ ነው፡፡ አፈጮሌ የኮንፈረንስ ስታሮች በነቢያትነት አገሪቷን ከዳር እስከ ዳር ናኝተውባታል፡፡ የህዝቡን ጀርባ እንዴት እንደሚያኩለትና እንደሚያስፈነድቁት አንደበታቸው ጥበቡን ተክኖታል፡፡ የህዝቡን ስሜት ኮርኩረው በደስታ ያሰክሩታል፡፡ ክፋቱ ስካሩ ከሰኞ ጠዋት ያለማለፉ እንጂ፡፡
መድረኩ እነዚህን ይፈልጋል፣ ካለበት እያሰሰ ለኮንፈረንስ ወረፋ ያስይዛቸዋል ፣Entertainment ነዋ! እሁድ ከሰአት የስጦታ ጊዜ ይባልና በጮሌ ምላስ ህዝቡን አስቤዛውን ያስተፉታል፡፡ መሪዎች ደስ ይሰኛሉ፡፡ በአመፀኝነት ለምናውቃቸው መሪዎች እንዴት ያለ አስደናቂ ቡራኬ፣ አድናቆትና፣ የትንቢት ድምጽ በማምጣት እኛንም በምቀኝነታችን ያሸማቅቁናል፡፡ እንዲህ ይቀለድና ዳጎስ ያለ ገንዘብ በፖስታ ተይዞ ይኬዳል፡፡ ለወደፊቱም ፕሮግራም አስይዞ፡፡
እውነተኛ ትንቢቶችና ራዕዮች የመኖራቸውን ያህል እንዲሁ ሀሰተኞች ደግሞ ከመድረክ እስከ ጓዳ የጴንጤውን ዓለም አጨናንቀውታል፡፡ እንደመደብር በየቦታው ቤተእምነት ለመፈልፈል፣ የማይፈልጉትን ሰው ስም ለማጥፋትና ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ፣የኮትሮባንድ ነጋዴዎችን ሳይቀር ለአመፀኞች ቡራኬ በመስጠት ከእነርሱ በሚገኘው ኑሮን ለመደጎም፣ አረ ስንቱ! ህዝቡም በዚህ ሱስ ተለክፎአል፡፡ ትላንት ተሸውዶ ዛሬም ይታለላል፡፡ እንደ ህመም ማስታገሻ ትንሽ ቅር ሲለው ሱሱን ለማስታገስ ይሮጣል፣ ይራወጣል፡፡ እረፍት አጥቶአል፡፡ እያሳደደ ገለባ ይበላል፡፡ ቃሉን / መፅሐፍ ቅዱስን / ስታስተምረው ወይም ስትሰብከው የፕሮግራም ማሟያ ስለሚመስለው አይሰማም፡፡ ያዛጋዋል፣ ያቁነጠንጠዋል፣ የለመደውን የሱስ ማስታገሻ ፍለጋ፡፡ እንግዲህ በአጭሩ ጴንጤነት ከቃሉ ይልቅ በትንቢት ላይ መመስረት ሆኖአል፡፡ ስለዚህ ወደ ቃሉ ካልተመለሰ ከስሮአል፡፡

No comments:

Post a Comment